የፕሮጀክት መርሲ መስራች ለነበሩት ለወ/ሮ ማርታ ገ/ፃዲቅ መታሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ ፡፡

ይህን ፕሮግራም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፕሮጀክት መርሲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በዚህም ፕሮግራም ላይ የባለስልጣን መስርያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሃላፊና ተወካዬች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የዚህም ፕሮግራም ዋና ዓላማ የPROJECT MERCY መሥራች ለነበሩት ወ/ሮ ማርታ ገ/ጻድቅ የሕይወት ጉዞ ለመዘከርና ሌጋሲያቸውን ለማስቀጠል ታስቦ መሆኑ ተገልጷል ፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ፕሮጀክት ሜርሲ የተመሰረተበት ዋነኛ ምክንያት የእለት ደራሽ ዕርዳታዎች ከማቅረብ ባለፈ በትምህርትና በጤና ስራ ላይ በርካታ ተግባራት በማከናወን የወገናቸውን ሕይወት ለመታደግ ነበር ብለዋል፡፡ ድርጅቱ መሰረቱ አሜሪካን ሃገር መሆኑን እና ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በሕጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከ25 ዓመታት በላይ መቆጠሩን ገልጸው በተለይ በደቡብ ብ/ብ/ሕዝቦች እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰታት የተቀናጀ የገጠር ልማት ስራ ላይ በተለይም በትምህርት፣ በጤና፣ በምግብ ዋስትና፣ በመሠረተ-ልማት እና የሙያ ክህሎትን በማዳበር ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡ እኚህ እናት በሰለጠነ ዓለም ውስጥ የመኖር ዕድል የነበራቸው ቢሆንም ለሀገራቸው ሕዝብ የነበራቸው ቀናዒ ልብ ፕሮጀክት ሜርሲን እንዲመሰርቱና ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ትተውልን አልፈዋል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የኘሮጀክት መርሲ መስራችና ባለራዕይ የነበሩት ወ/ሮ ማርታ ገ/ፃዲቅ በተወለዱ በ91 ዓመታቸው ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩንም ህያው ሥራቸው ግን ከኛ ጋር ይኖራል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ እኝህ ታላቅ እና የበጎ አድራጎት ሰው ለሰሯቸው በርካታ ተግባራትና ለአገራችን ላበረከቱት አስተዋጽኦ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት የተለያዩ ሽልማቶችና የዕውቅና ስጦታዎች በተለያየ ጊዜ መበርከቱን በመድረኩ ተገልጷል፡፡