የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በተገኙበት የትግራይ ሶሻል ኢንተርፕራዝ ምስረታ ተካሄደ፡፡

በትግራይ ብሄራዊ ክልል መቐለ ከተማ የትግራይ ሶሻል ኢንተርፕራይዝ ምስረታ ተካሂዷል፡፡ በምስረታው ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የክልሉ የማህበራዊ ልማትና ሽግግር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በምስረታው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ማህበራዊ ኢንተርፕራይዞችን የምትመራበት የህግ ማዕቀፍ እንደሌለ አንስተው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ይህ ህግ እንዲወጣ በባለቤትነት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የማህበራዊ ኢንተርፕራይዞች መቋቋምና መስፋፋት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከውጪ እርዳታ ተላቀው በሀገር ውስጥ ምንጭ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ሁነኛ መፍትሔ እንደሚሆኑ ጠቁመው የትግራይ ማህበራዊ ኢንተርፕራይዝ ምስረታ በሀገሪቱ ታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ማህበራዊ ኢንተርፕራይዝ ምስረታ ሀገሪቱ ከገባችበት ችግር ለመውጣት አስተዋጽዖው የጎላ እንደሆነ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ለኢንተርፕራይዙ ምስረታ አስተዋጽዖ ላደረጉ የክልሉ የሲማድ ህብረት /አክሶት/ እና ግለሰቦች ምስጋናቸውን አቅርበው ሀሳቡ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ማህበራዊ ኢንተርፕራይዞች የሚመሩበት ህግ እንዲወጣ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም አዲሱን አዋጅ 1113/2011 መሰረት በማድረግ የተዘጋጁ መመሪያዎች ላይ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ለትግራይ ክልል መልሶ ማቋቋም አይካፕ ኢትዮጵያ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ከ26 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መርጃ መሳሪያ አና አልባሳት ድጋፍ ተደርጓል፡፡