ሰላም፣ ፍቅር፣ እንክብካቤና ጥበቃ ለሁሉም ህጻናት በሚል መሪ ቃል በአገራችን ለ32ኛ ጊዜ የተከበረው የህጻናት ቀን ባስልጣን መስሪያቤቱ ከአሜን በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመሆን በድምቀት አከበረ፡፡
በበዓሉ ላይም የአሜን በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሀብቴ እንዳሉት የአሜን በጎ አድራጎት ድርጅት በ2011 ዓ.ም ሀያአምስት ህጻናትን ይዞ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አሜን በጎ አድራጎት (አሜን የፍቅር ቤተሰብ) ህጻናት ፈጽሞ አይለመንባቸውም፣ በልጆች ላይ መልካም ዘርን በመዝራት ተስፋ ያላት ኢትዮጵያን መፍጠር፣ ከማብላትና ከማጠጣት ያለፈ ስራ በአእምሮአቸው ላይ በመስራት ከጥገኝነት የተላቀቀ ሀገርሩን የሚወድ ቅን፣ የዋህ፣ ቸር በጎ አድራጊ ትውልድ ማፍራት፣ የሚሉ ዓላማዎች ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት የህጻናት ቀንን ከአሜን በጎ አድራት ድርጅት ጋር በማክበራችን ትልቅ ደስታ ይሰማናል ብለዋል፡፡
አያይዘውም መልካም ሀሳብ ይዞ የተነሳ ትውልድ ፍጻሜውም መልካም ይሆናል የተበላሸ ሀሳብ የያዘ ትውልድ ፍጻሜውም የተበላሸ ሊሆን ስለሚችል በህጻናት አስተሳሰብ ላይ መስራት እንደሚገባ አንስተው በተለይም በዲጂታል አለም እንዴት ህጻናት ሳይጎዱ ቴክኖሎጂን በአግባቡ ይጠቀሙ የሚለው ጉዳይ ላይ አጥብቀው መስራት ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዋናነት ዋና ዳይሬክተሩ አጽዕኖት ሰተው ያነሱት አገር በቀል ድርጅቶች የውጭ ድጋፍ ጠባቂ ሳይሆኑ በራሳቸው አቅም ህጻናትን ማሳደግ ሌሎች ማህበራዊ ችግሮቻቸውንም ለመቅረፍ በአገራችን ሀብት መስራት አለብን ሲሉ አንስተዋል፡፡
አዲሱ አዋጅ 1113/2011 ለድርጅቶች በርካታ የገቢ ማስገኛ ስራዎችን እንዲሰሩ እድሎች ተፈጥረዋል ይህ የሆነው በዋናነት አገራችንንም ሆነ ህዝባችንን ከውጭ እርዳታ በማላቀቅ በአገራቸው ሀብት እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ አሜን በጎ አድራጎት ድርጅት በስራ ላይ የገጠሙትን ችግሮች ባለስልጣን መስሪ ቤቱ በተቻለው አቅም ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡