የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ለህብረተሰብ ተጠቃሚነትና ለሀገር ልማት የላቀ አቅም መፍጠር እንዲችል ባለስልጣኑ እየሰራ እንደሚገኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ገለጹ፡፡


ወርልድ ሰርቭ ኢንተርናሽናል የተባለ የውጪ ድርጅት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በተገኙበት በሰሜን ሸዋ ዞን ባሶና ወራና ወረዳ እና በደብረብርሃን ከተማ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 10 በሶላር የሚሰሩ የውኃ ፕሮጀክቶችን አስመርቀዋል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የድርጅቱ የሀገር ውስጥ ተወካይ የሆኑት አቶ ከተማ ክንፈን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት እና የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የውሃ ፕሮጀክቶቹን ባስመረቁበት ወቅት እንዳሉት መንግስት ከፍተኛ የለውጥ ስራዎችን ከሰራባቸው ዘርፎች አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ እንደሆነ አንስተው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንም ዘርፉ ለህብረተሰብ የላቀ ተጠቃሚነትና ለሀገር ልማት የላቀ አቅም መፍጠር እንዲችል እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገር ሰላምና ግንባታ እያበረከቱ ያለው ድርሻ ትልቅ መሆኑን አንስተው ወርልድ ሰርቭ ኢንተርናሽናል በተለያዩ አካባቢዎች ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን በማከናወኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የተገነቡ የውሃ ፕሮጀክቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ማህበረሰቡ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የወርልድ ሰርቭ ኢንተርናሽናል የሀገር ውስጥ ተወካይ የሆኑት አቶ ከተማ ክንፈ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ የተሰሩት በማህበረሰቡ ተሳትፎ መሆኑን አንሰተው በቀጣይም ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 25 የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀግቶችን ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ውሃና ኢነርጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ሀይሌ ዳኛቸውና የደብረብርሃን ከተማ ውሃና ፍሳሽ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ መሰረት መንገሻ ድርጅቱ ለምረቃ የውኃ ፕሮጀክቶቹን ገንብቶ በማስረከቡ ምስጋናቸውን አቅርበው ፕሮጀክቶቹ ረጅም የአገልሎት ጊዜ እንዲኖራቸው በመንከባከብና በአግባቡ በመጠቀም የባለቤትነት ጥበቃ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብም ፕሮጀክቶቹ ለፍሬ በመብቃታቸው መደሰታቸውን የተናገሩ ሲሆን በአግባቡ እንደሚጠቀሙባቸውም ገልጸዋል፡፡