ኦርጋናይዜሽን ፎር ሰስተነብል ዴቬሎፕመንት (Organization for sustainable Development) በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል ድጋፍ አደረገ ፡፡

ኦርጋናይዜሽን ፎር ሰስተነብል ዴቬለሎፕመንት (Organization for sustainable Development) የተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሰርተፍኬት ቁጥር 2319 ተመዝግቦ በመንቀሳቀስ ያለ ድርጅት ሲሆን በአካባቢ ጥበቃ ፣በጤና፣ ትምህርትና አቅም ግንባታ ላይ መሰረት በማድረግ ይሰራል፡፡
ቀደም ሲል በሀገራችን ተከስቶ በነበረው ግጭት ከተለያዩ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል ለአንድ ሺ አምስት መቶ አባወራ የማብሰያ ቁሳቁሶችን፣ አልባሳትን፣ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ቁሳቁሶችን፣የብሎኬት ማምረቻ ማሽንን ጨምሮ የልብስ ስፌት ማሽን ድጋፍ አድርጓል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ አባተን ጨምሮ የባለስልጣን መ/ቤቱ የስራ ሃላፊዎች ፣የአፋር ክልል ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዎችና የኦርጋናይዜሽን ፎር ሰስተነብል ዴቬለሎፕመንት (Organization for sustainable Development) የቦርድ ዓባላትና የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ከድጋፍ መርኃ ግብሩ ጎን ለጎን ድርጅቱ በአፋር ክልል አሳኢታ ከተማ የገነባውን የጭስ አልባ ከሰል ማምረቻ ፕሮጀክት ለተሳታፊዎች ያስጎበኘ ሲሆን በዚህ ፕሮጀክት ከሃምሳ በላይ ለሚሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የቻለ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መሃመድ አህመድ ድርጅቱን በሚመለከት ባደረጉት ገለጻ ወጣቶቹ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ማሽኖችን ከውጭ ሀገር በማስመጣት የስልጠና እና የግብዓት ድጋፍ አድርገንላቸዋል ብለዋል ፡፡
የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ በበኩላቸው ድርጅቱ በልማቱ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመናገር በይበልጥ በአፋር ክልል ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ሰፋ ያለ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ፕሮጀክቱን በተጠናከረ መልኩ ለማስኬድና ከክልሉ ጋር በጋራ ተናቦ ለመስራት ተገቢው ድጋፍ ሊደረግ ይባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ አባተ በበኩላቸው ድርጅቱ ስላደረገው ድጋፍ አመስግነው ድርጅቱ የሚሰራቸው ፕሮጀክቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ከክልሉ አስፈጻሚ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበት እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በማስተሳሰር ዘላቂነቱ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡