ሀገራችን የማደግና የመልማት ህልሞቿን ለማሳካት እንደ አንድ የኢኮኖሚ ተዋናይ ከተቀበለቻቸው መካከል አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፍ ነው ተባለ፡፡

ቤዛ ፖስቴሪቲ ዴቬሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን የተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በሀገረ መንግስት ግንባታና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ግንዛቤ ማስጨበጥ ስልጠና በመስጠት ላይ ነው፡፡
በስልጠናው ላይ በክብር እግድነት የተገኙት የሲቪል ማህበሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ዘርፉን በተመለከተ በተከተለችው የተሳሳተ ፖሊሲ ከዚህ ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ መቅረቷን በማንሳት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሪፎርም ከተደረጉ ዘርፎች መካከል አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ በሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ በተለይም ጠንካራ ተቋማት እንዲፈጠሩ፤ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፤ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፤ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጉልህ ድርሻ አላቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ዘርፉ በአግባቡ ከተመራ የሲቪክ ባህሉ የዳበረ ማህበረሰብ እንዲገነባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል እና ዘርፉ ከስሜት ይልቅ በምክንያታዊነት የሚያምን፤ ለንግግርና ለውይይት ቅድሚያ የሚሰጥ ማህበረሰብ እንዲፈጠር በማድረግ ረገድም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
አያይዘውም የሀገር ልማት በጽኑ መሰረት ላይ መቆም የሚችለው የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በመተባበርና በመናበብ ህብረተሰቡን በማንቃት እንደሀገር የማደግ ተስፋችን ብሩህ ቢሆንም ሁሉም የህብረሰተብ ክፍል ለሀገሩ ልማትና ዕድገት ካልሰራ በስተቀር የምንፈለገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም፤ የውስጥ አቅማችንን በማጤን ያለንን ሀብትና ዕውቀት በመጠቀም ሀገራችንን ካለችበት ችግር ውስጥ ለማውጣት በመተማመንና በመተጋገዝ ስንሰራ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ከሰላም ሚኒስቴር የመጡት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ ለሰልጣኞች ባስተላለፉት መልዕክት አገራችን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባትና ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመጓዝ የውይይት መድረኮች አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመንግስት አካላት ጋር ተቀራርበው በመስራት የተለያዩ አገራትን ልምዶች በመቅሰም በጋራ ለማቀድ፣በጋራ ለመስራት ትልቅ እድል መፍጠር እንደሚቻል በማንሳት ቀድሞ የነበረው ህግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የገንዘብ ምንጫቸው ላይ ገደብ በማደረግ ብዙ ድርጅቶች ሊከስሙ መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
ቤዛ ፖስቴሪቲ ዴቬሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ እንዳሉት ድርጅቱ ሰባት በሚሆኑ ልበ ብርሃን በጎ ፈቃደኞች የተመሰረተ ሲሆን ዓላማውም በወቅቱ የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የነበረውን የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭት ለመቀነስና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት የተቋቋመ መሆንኑ በመግለጽ ድርጅቱ የእንቅስቃሴ አድማሱን በማስፋት በአሁኑ ጊዜ በጤና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሁም በሀገረ መንግስት ግንባታ እና በሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ውጤታማ ሥራዎቸን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡