የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለመካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች በስነ ምግባር፣ በፕሮፌሽናሊዝምና በሙስና ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለተቋሙ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች በስነ ምግባር፣ በፕሮፌሽናሊዝም እንዲሁም በሙስና ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና እየሰጠ ሲሆን በስልጠናው ላይ የሁሉም ስራ ክፍል ሃላፊዎችና የዴስክ ሃላፊዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
በመርኃ ግብሩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ አመራር ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው እንዳሉት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሁለተኛው ተቋማዊ ለውጥ ሂደት ውስጥ ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች የውስጥ አቅም ማሳደግ አንዱ እንደሆነ አንስተው በስነ ምግባር የታነጸ ብቁ የሰው ኃይል እንዲኖር የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የተቋሙን የስትራቴጂክ እቅድ ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያነሱት አቶ ተስፋዬ በተለይም የተቋሙ ሰራተኞች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ራስን መመልከትና ስነ ምግባርን መላበስ እንዲሁም በቅንነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የስነምግባር መከታተያ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት አቡዬ በበኩላቸው ስልጠናው ለሁሉም የተቋሙ ሰራተኞች በተከታታይ ለአራት ዙር ሲሰጥ መቆየቱን አንስተው ሰራተኞች የሚሰጡት አገልግሎት ውጤታማ እንዲሆንና ከሙስና የጸዳ እንዲሆን የሚያስችል ስልጠና መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሰራተኞቹን በአዲስ መልክ ካደራጀበት ህዳር ወር ጀምሮ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለተቋሙ ሰራተኞች በመስጠት የውስጥ አቅሙን በማሳደግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለይም የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ከብልሹ አሰራር የጸዳና ተቋሙ የሚታወቅበትን ቀልጣፋ አሰራር ለማላቅ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡