የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ አፈጻጸም ማስመዝገቡ ተገለጸ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድጅቶች ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸማቸውን የገመገሙ ሲሆን በዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እንደተመላከተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ካለፈው ተመሳሳይ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል እንደታየበት ተገልጿል፡፡ የድርጅቶችን ምዝገባ በሚመለከት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 474 አገር በቀል እና 43 የውጭ ድርጅቶች በድምሩ 517 ድርጅቶች መመዝገቡን እንዲሁም 161 ድርጅቶች በምዝገባ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በሃምሳ ድርጅቶች (50) አብላጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዳግም ምዝገባ ያደረጉ 100 ድርጅቶች ሲሆኑ በዳግም ምዝገባ ሂደት ላይ የሚገኙ ድርጅቶችም 58 መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
2113 ድርጅቶችን በዴስክ ኦዲት ለመድረስ እቅድ ተይዞ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 2100 ድርጅቶች የዴስክ ኦዲት የተደረገላቸው ሲሆን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ33.35 ከመቶ ብልጫ እንዳለው ያሳያል፡፡ በሪፖርቱ 20/80 ባላሟሉ ድርጅቶች ላይ ግብረመልስ ከመስጠት ጀምሮ የድርጅቶቹ ኃላፊዎች ቀርበው እንዲያስረዱ እንዲሁም የተጓደሉ ማስረጃዎችን እንዲያቀርቡ የሚያስገድዱ ርምጃዎች መወሰዳቸው ተገልጿል፡፡ በመስክ ክትትል የተደረገባቸው 389 ድርጅቶች ሲሆኑ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ140 ድርጅቶች ብልጫ ያለው መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በጠቅላላው የመስክና የዴስክ ኦዲት ከተደረጉ 2,489 ድርጅቶች ውስጥ ለ1883 (75.65%) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ግብረ መልስ የተሰጠ ሲሆን ካለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በዚህ በጀት አመት በ995 (47.16%) ድርጅቶች ብልጫ እንዳለው ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
በሪፖርቱ ጥሩ አፈጻጸም ታይቶባቸዋል ከተባሉባቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅን መሰረት አድርገው በወጡ መመሪያዎች ላይ የተሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ ከክልል እና ባለድርሻ እንዲሁም ከአጋር አካላት ጋር ትብብር መጠናከሩ፣ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በተያያዘ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሂደት ስኬታማ ሂደት ላይ መገኘቱ፣ እንዲሁም የተቋሙን ውስጣዊ የአፈጻጸም አቅምን ማጎልበት መቻሉ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከነዚህ በተጨማሪም የተገልጋይ እርካታ መሻሻል የታየበት እንደሆነና ብልሹ አሰራርንና የስነምግባር መጓደል የሚያስከትሉ ጉዳዮችን በሚመለከት ለተቋሙ ሰራተኞች የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች መሰጠታቸው እንደመልካም አፈጻጸም ከተነሱት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባለፉት ዘጠኝ ወራት የታዩ ስኬታማ አፈጻጸሞች ቀጣይነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ክፍተት ናቸው ተብለው በሪፖርቱ የቀረቡ ጉዳዮች በቀጣዮቹ ሶስት ወራት እንዲቀረፉ በትጋትና በሙሉ አቅም መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡ በተለይም በሂደት ላይ ያሉ ስራዎች ሲጠናቀቁ የተቋሙን አፈጻጸም በእጅጉ የሚያሻሽሉ ስለሆነ ከምንግዜውም በላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሁለተኛው የለውጥ ሂደት ላይ እንደመገኘቱ ስኬታማ ስራዎቻችንን ማጽናት፤ ማላቅና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማገዝ ይገባናል ያሉ ሲሆን የታዩት አፈጻጸሞቻችን ጥሩ ናቸው በቀጣይ ግን የበለጠ ስኬታማ ለመሆን በትጋት መስራት እንደሚጠበቅ አንስተዋል፡፡