በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ቻይናውያን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት አቋቁመው ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚፈልጉ ገለጹ፡፡

በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚሰሩ በርካታ ቻይናውያን በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት አቋቁመው መንቀሳቀስ እንደሚፈልጉ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ጋር ባደረጉት ውይይት ገልጸዋል፡፡  ውይይቱን ያደረጉት ከቻይና ኤምባሲ የመጡ የስራ ኃላፊዎችና ሩሎ ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን የተባለ በቻይና ሀገር የሚንቀሳቀስ ድርጅት ኃላፊዎች ናቸው፡፡ በርካታ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መንቀሳቀስ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ግን የምዝገባ ሂደቱ ምን እንደሆነ በቂ መረጃ የለንም ያሉት ተወካዮቹ በተለይም ለረጅም ጊዜ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ቻይናውያን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ማቋቋም ይይልጋሉ ብለዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ለኤምባሲው ተወካዮችና ለሩሎ ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን ሃላፊዎች ስለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባ እና አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት በማድረግ ማሟላት ስለሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ድርጅቶች የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት አድርገው እንዲሰሩ እንፈልጋለን በዚህ ረገድ ቻይናውያን በኢትዮጵያ የማህበረሰቡን ችግር መሰረት ያደረጉ ስራዎችን ስለሚሰሩ ትልቅ አክብሮት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ቻይናውያኑ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መጥተው መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን አንስተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከቻይና ለሚመጡም ሆነ እዚሁ አገር ሆነው መመዝገብ ለሚፈልጉ አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል ብለዋል፡፡