የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስጣን ከማሪ ስቶፕስ ኢንትርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሴት ሰራተኞች በአመራር ክህሎት ላይ ስልጠና ሰጠ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከማሪ ስቶፕስ ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሴት ሰራተኞች በአመራር ጥበብና ስራ አመራር ክህሎት ዙሪያ ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚቆይ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በስልጠና መርኃግብሩ ላይ የተገኙት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ስኬታማና ምሳሌ የሚሆን ተቋም እንዲሆን የተለወጠ እና ተነሳሽነት ያለው የሰው ኃይል ያስፈልገዋል ለዚህም ከድርጅቶች ጋር መርህን መሰረት ባደረገ ግንኙነት ላይ ተመስርተን በትብብር ስልጠናዎችን እየሰጠን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሚሰጡ ስልጠናዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ለመለወጥ የሚያስችልና ውጤቱም የሚበረታታ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ የተለወጠና የነቃ የሰው ሃይል እንዲኖረን ራስን መለወጥና በራሳችን ላይ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሴቶች ላይ ያልዋዠቀና የጸና ትልቅ እምነት አለው ያሉ ሲሆን የተሰጣቸውን ስራ በአግባቡ የሚወጡ ስኬታማ ሴት ሰራተኞች እንዳሉም ጠቅሰው ቁጥራቸው ከፍ እንዲልና ሙሉ አቅማቸውን እንዲያሳዩ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ ማሪ ስቶፕስ የሀገር ውስጥ ተወካይ ዶ/ር አበበ አሸብር በበኩላቸው ሴቶችን ውኃ በማይቋጥር ምክንያት ወደፊት እንዲመጡ ማድረግ ባለመቻላችን ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል ያሉ ሲሆን ማሪ ስቶፕስ በቀጣዮቹ ሶስትና አምስት አመታት ሴቶችን ቢያንስ 50 ከመቶ ሴቶችን ወደአመራር ለማምጣት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን ለሴቶች የተመቸ የስራ አካባቢ ከማድረግ አንጻር ሴቶች ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት ዶ/ር አበበ ይህ ስልጠና የሴቶችን ተደማጭነት ለማስፋት እንዲሁም እርስ በርስ የሚደጋገፉበትንና ወደፊት የሚመጡበትን አቅጣጫ የሚጠቁም እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ስልጠናውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል ጋር በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን ሴተር ፎር ክርኤቲቭ ሊደርሽፕ (center for creative leadership) ደግሞ ስልጠናውን የሚሰጠው ተቋም ነው፡፡