በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የጋራ ትብብር እየተካሄደ የሚገኘው የሚዲያ አካላት የመስክ ጉብኝት 3ኛ ቀኑን ይዟል፡፡
የሚዲያ ቡድኑ በ3ኛ ቀን የመስክ ምልከታው አዎንታዊ ምላሽ ለልማት (PAD) የተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በታዳሽ ሃይል ላይ ወጣቶችን አሰልጥኖና አደራጅቶ እየሰራ የሚገኘውን ስራ እንዲሁም ዎርልድ ቪዥን (world vision) የተባለ የውጭ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በቁጠባ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ያከናወናቸውን ተግባራት ተመልክቷል፡፡ ጉብኝቱ የተካሄደው በምስራቅ ሀረርጌ ዞን መልካ ጀልዱ ቀበሌ እንዲሁም በአወዳይ ከተማ እና በሀረሪ ክልል ሃኪም ጋራ ላይ በዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎች የታዩ ሲሆን በእነዚህ ቦታዎች በተለይም በጃርሶ አካባቢ ፕሮግራም 72.523 እና በቡርቃ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት 54.984 የማህበረሰብ ክፍሎችን እንዲሁም አዎንታዊ ምላሽ ለልማት (PAD) በተባለው ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በአወዳይ ከተማ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራ ላይ ለተሰማሩ በሁለት ማህበራት ለተደራጁ 60 ከስደት ተመላሽ የማህበረሰብ ክፍሎች ቋሚ የስራ እድል በመፍጠር በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የቻሉ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ በጉብኝቱ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በድርጅቶቹ ስራዎች መደሰታቸውን ገልጸው መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ በቅንጅት ሲሰሩ ለሀገር ልማትም ሆነ ለህብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው የቡርቃ ኢኒሼቲቭ ፕሮጀክት ትልቅ ማሳያ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው በመልካ ጅልዱ ትምህርት ቤት እንዲሁም በሀኪም ጋራ የተሰሩ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ፕሮጀክቶች ማህበረሰቡን ያሳተፉ መሆናቸው እና ውጤታማ እንደሆኑ መመልከታቸውን ጠቅሰው የፕሮጀክቶቹ ዘላቂነት ለማስቀጠል ድርጅቶቹ የሄዱበት የአሳታፊነት መንገድ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡