7ተኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የክልል እና የፌደራል ባለድርሻ አካላት ጉባኤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ በተገኙበት በድምቀት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ቢሮ ሃላፊዎች የሁሉም ክልል የፋይናንስ አና ፍትህ ቢሮ ሃላፊዎችና የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕረዝዳንት ተገኝተዋል፡፡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ በንግግራቸው እንደገለጹት ይህ የጋራ ጉባኤ በክልላችን ለማድረግ ስለመጣችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው በማለት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሪፎርም ስራዎች ከተሰራባቸው የህግ ማዕቀፍ ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ አንዱ ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም ለውጡን ተከትሎ በአገራችን የሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እያደረጉት ያለው እንቅቃሴ የተሻለ መሆኑን ገልፀው የክልል መንግስታትና የፌደራል መንግስት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት በክልሉ የሚሰሩ ድርጅቶች በአግባቡ በመያዝ እንዲሁም አዳዲስ ድርጅቶችንም ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ገልፀዋል፡፡ የኢፌዲሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ዓለም ዓንተ አግደው በንግግራቸው እንደገለጹት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ፣የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ሥራ እና የሽግግር ፍትህን አላማ ለማሳካት እንዲሁም መንግስት የጀመረዉን የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና ሙስናን የመታገል ዘመቻ የተሳካና ዉጤታማ ለማድረግ የሁሉንም አካላት የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ ሲሆን በተለይም ለትርፍ ያልተቋቋሙትና ለፖለቲካ ያለወገኑት የስቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነዉ ብለዋል፡፡
ከምንገኝበት ወሳኝ የአገር ግንባታ ምዕራፍ አንጻር በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም የህግ የበላይነትን በማረገጋገጥ፣ሰላምን በማስፈን፣ግጭቶችን በዘላቂነት በመፍታት እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ሂደት የሲማዶች ከእስከአሁኑ በበለጠና ትርጉም ባለዉ መልኩ አወንታዊ ሚናችሁን መጫዎት ይኖርባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የስቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲያሳኩ በመደገፍ፣በመከታተልና በመቆጣጠር ኃላፊነት ያለባችሁ አካላት ባለስልጣን መ/ቤቱን ጨምሮ ፤ የፌዴራል፣የክልልና ከተማ አስተዳደሮች በተለይም የፍትሕና የፋይናንስ ቢሮዎች አገራችን ከዘርፉ የበለጠ መጠቀም እንድትችል ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት መንቀሳቀስ ይኖርባችኋል በማለት በቋሚነት የሚካሄደውን የጋራ ጉባኤ አመስግነዋል፡፡ አቶ ጂማ ዲልቦ የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለመውሰድ ባለፉት አምስት አመታት በርካታ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን እና እየተካሄደ ያለው የሪፎርም ንቅናቄ የዘመናት የኢትዮጵያውያን መሻት እና የታሪካችን አካል መሆኑን አንስተዋል፡፡ የተገኙ አገራዊ ስኬቶችን አስጠብቆ የማስቀጠልም ሆነ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለማለፍ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ሚናው የማይተካ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ ሂደት የሲማዶች ሚና የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በመታመኑ መንግስት ሲማዶችን ከሦስቱ የኢኮኖሚ ተዋናዮች መካከል አንደ አንዱ በመውሰድ ምቹ የእንቅስቃሴ ምህዳር እንዲፈጠርላቸው የህግና የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
7ተኛውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣የክልል እና የፌደራል ባለድርሻ አካላት ጉባኤ ልዩ ከሚያደርጋቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደ ተቋም የመጀመሪያውን የሪፎርም ምዕራፍ በማጠናቀቅ 2ኛውን ተቋማዊ ሪፎርም በጀመርንበት ማግስት የሚካሄድ መሆኑ ነው፤ 2ኛው ተቋማዊ የሪፎርም አቅጣጫችን በመጀመሪያው የሪፎርም ምዕራፍ ያገኘናቸውን ውጤቶች ከማጽናትና ከማላቅ ባሻገር የአገልግሎት አሰጣጣችንን ማዘመንና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በዘርፉ እንዲተገበር ማስቻል፤ በምናከውናቸው ቀጣይ ስራዎች ስፔሻላይዜሽን ላይ ትኩረት በማድረግ የሲማድን አስተዋፅኦ እንዲልቅ ማድረግ፤ ዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ ለአገር ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያውል የትብብርና የአጋርነት መንፈስን አጠናክሮ ማስቀጠል፤ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ በሁሉም ሴክተሮችና ተቋሞች አጠናክሮ ማስቀጠል፤ በየሴክተሩ የጋራ የምክክር ፎረሞችን በማደራጀት ልምድ መለዋወጥ፣ አፈፃፀሞችን መገምገም፣ ችግሮችን መለየት፣ መፍትሄዎችን መተለም፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡