ከህዝብ ተወካዬች ምክር ቤት ከህግና ፍትህ ጉዳዬች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ውይይት ተደረገ፡፡
ውይይቱ በባለፉት አራት ዓመታት በዘርፉ የተካሄዱ የህግ እና ተቋማዊ ሪፎርም ዙሪያ ሲሆን በመድረኩ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱን ጨምሮ ሁሉም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተገኝተዋል፡፡ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት በሀገራችን ኢትዮጵያ በወርሀ መጋቢት 2010 ዓ.ም የተደረገው ሀገራዊ ለውጥ ከዳሰሳቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገትና ልማት፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፤ በአጠቃላይ ለሀገረ መንግስት ግንባታና ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወቱ በመታመኑ ከመንግስትና ከግሉ ሴክተር ጎን ለጎን እንደ አንድ የልማት ተዋናይ ተወስደዋል ብለዋል፡፡
ድርጅቶቹ ለሀገር ልማት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ አዲስ ሕግ አውጥቶ ሥራ ላይ ከማዋል ጎን ለጎን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተከታታይ የሪፎርም ተግባራት በማከናወን ባለፉት ሦስት ዓመታት አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡
የመድረኩ ዓላማም በዚህ ዘርፍ ውስጥ የተደረጉ የህግና የአሰራር ሪፎሞችን ለመቃኘትና ባለሥልጣኑ ባለፉት አራት የሪፎም ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት ለተከበረው የህግና የፍትህ ቋሚ ኮሚቴ በማስተዋወቅ የሥራ መመሪያ ለመቀበል መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የህዝብ ተወካዬች ምክርቤት የህግና ፍትህ ጉዳዬች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ በንግግራቸው እንደገለጹት ሃገራችን በባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ሪፎርም አከናውናለች ሪፎርም ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አንዱ ነው፤ ተቋምን መገንት ደግሞ ሃገርን መገንባት በመሆኑ መልካም ጅምሮች መመልከት ተችሏል ብለዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም ተቋሙ ያከናወናቸው ተግባራት ፣ያጋጠሙ ችግሮችና ቋሚ ኮሚቴው ማገዝ ስለሚገባቸው ጉዳዬች ውይይት በማድረግ እና የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የክትትልና ቁጥጥር ስራውን ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡