በሳቢን ባካዮና ካንዚ የሚመራው የቡርኪናፋሶ ሉዑካን ቡድን ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር የልምምድ ልውውጥ አካሄደ::

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በኢትዮጵያ የሚገኘው የቡርኪናፋሶ ኢምባሲ አስተባባሪነት ከቡርኪናፋሶ የመጣው ሉዑካን ቡድን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና በዘርፉ ላይ የተደረገውን ለውጥ (reform) አስመልክቶ የልምምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ በልምድ ልውውጡ ላይ የተገኙት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ለልዑካን ቡድኑ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በዘርፉ ላይ የታየውን ለውጥ በማስመልከት ገለጻ አድርገዋል፡፡ በገለጻቸውም እንዳሉት በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 ከፀደቀ በኋላ በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን በማንሳት ለአብነት ያህል አገልግሎቶች በኦንላይ መሰጠታቸውን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ም/ቤት መቋቋሙ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ አስተዳደር መቋቋሙ፣ ለዘርፉ ሰፊ ምዕርዳር መፈጠሩን እና ሌሎችም በርካታ ስራዎችን ለልዑካን ቡድኑ ገልፀዋል፡፡ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አፍሪካውያን ተመሳሳይ ባህል ስላላቸው የእርስ በእርስ የልምምድ ልውውጥ ማድረጋቸው ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም ለመፍታት እንደሚያግዝ በመግለጽ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል፡፡
በመጨረሻም የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ወደኢትዮጵያ በመምጣታቸው ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳቢን ባካዮና ካንዚ እንዳሉት የተደረገላቸው አቀባበልና የተደረገላቸውን ገለጻ በማመስገን በቀጣይ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ አንስተዋል፡፡