የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በእውቀትም በአመለካከትም ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅ ተጠቆመ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በቢሾፍቱ ከተማ ለተቋሙ ባለሙያዎች ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ስልጠናዎቹ ትኩረት ያደረጉት በቡድን ስራ፣ በስራ አመራር፣ የስራ ግንኙነት እና ከጥቃት ጥበቃ እንዲሁም አዋጅ ቁጥር 1113/11 መሰረት አድርገው በወጡ መመሪያዎች (team building, leadership, communication, safeguarding, directives) ዙሪያ ነው፡፡ በእለቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ለሰልጣኝ ባለሙያዎች ባስተላለፉት መልዕክት ሁለተኛው ተቋማዊ ሪፎርም ከተጀመረ ወዲህ አሰራርን ከመዘርጋት ባለፈ የበለጠ አቅምን ሊገነቡ የሚችሉ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን አንስተው በዚህም አበረታታች ውጤት እየተመዘገበ እንደሆነ መረዳት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን ተቋማዊ ሪፎርም ውጤታማ ለማድረግ ስልጠናዎቹ መዘጋጀታቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተቋሙ ባለሙያዎች በእውቀትም በአመለካከትም ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አንስተው ለዚህም ዝግጁነት ይህ ስልጠና በእጅጉ የሚጠቅም መሆኑን አንስተዋል፡፡ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሚሰጣቸው ስልጠናዎች የራስን አቅም በመገንባት ለተቋም ለውጥ አስተዋጽዖ በማድረግ የተግባር ሰው መሆን የሚጠበቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በቅርቡ መዋቅራዊ አደረጃጀት በመስራት ወደ ሁለተኛው የሪፎርም ስራ ከገባ በኋላ ስኬታማ ውጤት ለማስመዝገብ በየደረጃው ለሚገኙ የተቋሙ አመራሮችና ባለሙያዎች በርካታ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡