የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት አድርገው በወጡ መመርያዎች ዙሪያ የሚሰጠው ስልጠና በሁሉም ክልሎች እና የክልል ዞኖች አጠናክሮ ቀጥሏል ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በኮምቦልቻ እና በሻሸመኔ ከተማ እና አከባቢው ለሚገኙ የመንግስት ባለድርሻ አካላት እና በአከባቢው ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ጋር በመተባበር በጸደቁ ስድስት መመሪያዎች ዙሪያ ለዞን መምሪያ ኃላፊዎችና ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኮምቦልቻ ከተማ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ በዞኑ ለሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም በዞኑ ለሚገኙ የመንግስት ባለድርሻ አካላት ከኦሮሚያ ገንዘብ ቢሮ ጋር በመተባበር ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡
በኮምቦልቻ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር ደመቀ ቦሩ ስልጠናው ሲታሰብ በክልል ደረጃ እንዲደረግ የታሰበ ቢሆንም በዞን ደረጃ ስልጠናው እንዲሰጥና እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ስለመመሪያዎቹ ግንዛቤ እንዲፈጠር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ላደረገው ቀና ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበው በቅንጅትና በህብረት መስራት እንደዚህ አይነት እድሎችን እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡
ደሴ፣ ኮምቦልቻና ደቡብ ወሎ በመቀናጀታቸው የተሻለ አፈጻጸም አይተናል ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በክልል ደረጃ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲኖሩንና ፕሮጀክቶች እንዲሰፉ እንፈልጋለን ያሉ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡ አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ችግሮችን የሚፈቱ ጉድለቶችን የሚሞሉ አጋዦች በመሆናቸው እስካሁን የነበረውን የተዛባ እሳቤ ማውጣት አለብን ያሉ ሲሆን እንደ አመራር የሚገጥማቸውን ተቋማዊም ሆነ የህግና የአሰራር ችግር ሊቀረፍላቸው እንደሚገባ አንስተው ወደክልሉ የሚመጡ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ፈንድ አስተዳደር እና የሲ.ማ.ድ ንብረት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለማሪያም አየለ በበኩላቸው የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የምንችለው ለማህበረሰቡ ችግር ቅድሚያ በመስጠት፣ ልማቱን ሊያፋጥን፣ ችግሮቹን ሊፈታ በሚችል መልኩ ከመንግስት አሰራር ጋር በማስተሳሰር መስራት ሲቻል መሆኑን አንስተው መመሪያዎቹ የተዘጋጁትም በአሰራር ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በማለም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሻመኔ ከተማ በምዕራብ አርሲ ዞን ለሚገኙ የመንግስት ባለድርሻ አካላት እንዲሁም በዞኑ ለሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተሰጠው ተመሳሳይ ስልጠና ላይ የተገኙት በኦሮሚያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ዴቢሳ በሃገራችን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለረጅም ዓመታት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው አዋጅ ቁጥር 621/2001 የህብረተሰቡን የመደራጀት መብትን የሚገድብ ስለነበር በልማቱና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት አዳጋች እንደነበር ተናግረዋል ፡፡
ከለውጡ በኋላ መንግስት ቀደም ሲል የነበረውን አዋጅ ሙሉ በሙሉ በማሻሻል የህብረተሰቡን የመደራጀት መብት ክፍት በማድረጉ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና መልካም አስተዳደር ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ለማበርከት ችለዋል ብለዋል ፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሁሉም ክልሎችና ዞኖች ጭምር በአዲሱ አዋጅ 1113/2011 እና አዋጁን ተከትሎ በወጡ መመርያዎች ላይ የግንዘቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እየሰጠ መሆኑን ያነሱት አቶ ፍቃዱ እንደክልል ከዚህ ቀደም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚበዙበትና ጥሩ እንቅስቃሴ ያለበትን ዞን በመለየት ለሁለት ዙር በአዋጁና እሱን ተከትለው በወጡ መመርያዎች ላይ ስልጠና መሰጠቱን እንዲሁም በቀጣይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በብዛት በሚገኙባቸው ዞኖች የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከክልል ገንዘብ ቢሮዎች ጋር በመተባበር አዋጁን ለማስፈጸም የወጡ መመሪያዎችን ከክልል እስከ ዞን ለሚገኙ ባለድርሻ የመንግስት አካላት እንዲሁም በየክልሉ ለሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በቅርበት ስልጠናዎችን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይም ስልጠናው ባልተዳረሰባቸው ክልሎችና ዞኖች መሰጠቱን የሚቀጥል ይሆናል፡፡