በጸደቁ መመሪያዎች ዙሪያ ለተቋሙ የማኔጅመንት አባላት እና ቡድን መሪዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በስልጠናው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በሪፎርም ሂደቱ ውጤታማ ለመሆን ለተቋሙ አመራርና ሰራተኞች በርካታ ስልጠና መሰጠቱን አንስተው እውቀት በየግዜው የሚሻሻልና የሚያድግ በመሆኑ ሁልግዜ ስልጠና መውሰድ፣ማንበብ እና እራስን ማብቃት (update ) ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ተቋሙ በመጀመሪያው የሪፎርም ምዕራፍ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ በማለፍ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን አስታውሰው በአዲስ መነሳሳት የተጀመረው ሁለተኛው ተቋማዊ ሪፎርም እውቀትን መሰረት ያደረገ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ተቋም መገንባት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ብለዋል፡፡ ያለእውቀት የሚከናወን ተግባር ውጤታማ አያደርግም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ሁሉም በሚሰራበት ስራ ዘርፍ ህጎችን፣መመሪያዎችን፣ ደንቦችን ማስተር ማድረግ እና እውቀትን መሰረት ያደረገ አገልግሎት መስጠት ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም እደተቋም አንዱ የተሰጠን ተግባርና ሃላፊነት ድርጅቶች የሚሰሯቸውን ስራዎች ከመንግስት ፖሊሲ ጋር የተጣጣሙ እንዲሆን ማድረግ ሲሆን ይህንን ለማስፈጻም ተቋሙ የተቋቋመበትን አዋጅ እና የወጡ መመሪያዎችን በአግባቡ ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡