በፌደራል ደረጃ የተዘጋጀው የመንግስትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ጉባዔ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድጅቶች ባለስልጣን ከሲቪል ማ ኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ጋር በመተባበር በፌደራል ደረጃ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ጉባዔ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በጋራ ጉባዔው ላይ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳተፊ ሆነዋል፡፡
የፍትህ ሚንስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በሀገራችን ያለው ሀብት ውስን በመሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዚህ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመገንዘብ አገልግሎታቸው የተሳለጠ እንዲሆን በክልል ደረጃ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ መድረክ ተመስርቶ ላለፉት ዓመታት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማጎልበት አንጻር ሲያሳልጥ መቆየቱ አንስተዋል፡፡
አክለውም መድረኩ ይህንን ትብብር ወደላቀ ደረጃ የሚያደርስ፣ በውስን የሰው ሃይል እና የፋይናንስ አቅም ያለውን አስተባብሮ የሚያሰራ ፣ያለውን ውስን ሀብት በተናጠል ከመስራት ይልቅ ለጋራ ዓላማ በተገናዘበ መንገድ በትብብር ለመስራት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ የዜጎችን ጥቅም ለማረጋገጥ ከፌደራል መንግስት ተቋማት ጋር በመተባበር በመስራት የማይተካ ሚናችሁን እንደምትወጡ እና ከዚህ መድረክ ምስረታ በኋላ ወቅታዊ ግንኙነቶችን በማድረግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ እንደምታደርሱ እምነቴ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው የመድረኩ ዓላማ በፌዴራል መንግስቱ የሚመለከታቸው አካላትና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነትና ትብብር በማጠናከር በዘርፉ ያለውን ጠንካራና ደካማ ጎን በመለየት የሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት ከዘርፉ ጋር በቅርበት በመሥራት የሀገራችንን ብልጽግና በማፋጠን ውስጥ ዘርፉ ሊጫወት የሚገባውን ሚና እንዲጫወት ማድረግ የመድረኩ አላማ መሆኑን አንስተው የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ መድረክ በክልሎች የተለመደና በተለይም በባለፉት አመታት እየተጠናከረ የመጣና ውጤት እያስመዘገበ ያለ ፎረም መሆኑን አንስተዋል፡፡
የምክክር መድረኩ በፌዴራል ደረጃ ለማቋቋም ጥረቶች ሲደረጉ ቆይቶ በተለያዩ ምክንያቶች ቢዘገይም አሁን መቋቋሙን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ቀደም ሲል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከፌዴራልና ከክልል አስፈጻሚ አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት ውጤታማ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ እና አሁን በፌዴራል ደረጃ የሚመሰረተው መድረክም ዘርፉን ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለመምራት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ መለሰ በበኩላቸው ሃገራችን አሁን የምትገኝበትን አስቸጋሪ የደህንነት ሁኔታ ተሻግራ ዘለቂ ሰላምን እንድታረጋግጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እና የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ያሉ ሲሆን በተለይም የዘላቂ ሰላም መሰረቶች አንዲጣሉ፤ ግጭቶችን በሰለጠነ መንገድ እና በውይይት የመፍታት ባህል ስር እንዲሰድ ፤ አካታችነት እና መቻቻል እንዲጠናከር፤ በአጭሩ የሰላም ባህል በሀገራችን እንዲስፋፋ እና የበላይነት እንዲኖረው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፕሮጀክቶችን በመቅርፅ መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በፌደራል ደረጃ የተዘጋጀው የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ጉባኤ ዛሬ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በመድረኩ ላይ የተለያዩ መነሻ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡