የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላም፣በዲሞክራሲ፣በሃገረ መንግስት ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ውስጥ አይነተኛ ሚና እንዳላቸው ተገለጸ፡፡

የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አጋርነትና ትብብር ለሃገር ግንባታ ያለው ሚና በሚል ርዕስ ሰብዓዊ መብት ላይ ከሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በመክፈቻ ንግግራው እንደገለጹት ተቋሙ በሃገራዊ ሪፎርም ውስጥ ካለፉ ተቋማት መካከል መሆኑን አንስተው ድርጅቶች የሃገረ መንግስት ግንባታው ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ የሚያስችል መሰረታዊ ስራዎች በባለስልጣን መስሪያቤቱ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ መድረኩ ስለፌዴሬሽን ምክርቤቱ ግንዛቤ በመያዝ በጋራ መስራት ስለሚገቡ ጉዳዬች ለመወያየት እድል እንደሚሰጥ ጠቅሰው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላም ፣በዲሞክራሲ፣በሃገረ መንግስት ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ውስጥ አይነተኛ ሚና አላቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንደገለጹት የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ዘርፈ ብዙ የእንቅስቃሴ መስክ ያላቸው መሆኑን አንስተው ይኸውም ዜጎችን ከማንኛውም ጥቃት ከመከላከል ጀምሮ ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመድረስ እንዲሁም ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን በሕገ መንግስቱ የተረጋገጡ የዜጎች መብቶች እንዲከበሩ የሙግት ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡
የመድረኩን ዓላማ ሲያብራሩ በሕገ መንግስቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል ከሆነው ፣ ሕገ መንግስትን የመተርጎምና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ የማድረግ ሥልጣን ከተሰጠው እና በህዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲዳብር የማድረግ ሥልጣን ከተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አብረው ሊሰሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ለመመካከርና የጋራ ግንዘቤ በመጨበጥ ተግባራዊ እርምጃዎች ለመውሰድ እንዲቻል ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ መድረኩ በጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ አንደሚያበረክት ይታመናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከፌዴራልና ከክልል አስፈጻሚ አካላት ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት ውጤታማ ሥራዎች በማከናወን ለይ ያለ ተቋም እንደመሆኑ መጠን አሁንም ከፌዴሬሽን ምክርቤት ጋር የጀመርነውን ግንኙነት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አጋርነትና ትብብር ለሃገር ግንባታ በሚል ርዕስ እንዲሁም አቶ በላይ ወዲሻ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ም/ጽ/ቤት ሃላፊ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስታዊ ተልዕኮና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና በሚል ርዕስ ሰነድ አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የውይይት መድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ሰላም ኢንስቲቲዩት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡