ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሰራተኞችና ባለሙያዎች በዓይነ ስውራን ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብር ተካሄደ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከቱጌዘር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለተቋሙ ሰራተኞችና ባለሙያዎች ለአይነ ስውራን ስለሚደረግ ድጋፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አካሂዷል፡፡ በዚህ በመርኃ ግብር ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ምክትል ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባደረጉት ንግግር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በደረገው የመዋቅር ለውጥ አካል ጉዳተኞች በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር እንደዘረጋ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም ይህ ፕሮግራም የተዘጋጀው አካል ጉዳተኞች በተለይም አይነስውራን የሚገጥማቸው ችግር ምን ያህል ትልቅ እንደሆነና ስሜታቸውን እንድንጋራ እንዲሁም በያለንበት የሃላፊነት ደረጃ መወጣት ያለብንን ግዴታ እንድንገነዘብ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
የቱጌዘር ኢትዮጵያ ስራስፈጻሚ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ ለዓይነ ስውራን የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግና በዓይነ ስውርነት ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2013 የተቋቋመ መሆኑን አንስተው እስካሁንም በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ በመርኃ ግብሩ ላይ ውይይት እና የጨለማ ሂወት ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ዝግጅት የቀረበ ሲሆን የህይወት ተመክሮ ቀርቧል::