በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የተዘጋጀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ላይ ግብዓት የማሰባሰቢያ መድረክ ተዘጋጀ፡፡

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያስተላለፉት የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ እንደገለጹት 90 ፐርሰንት በሚባል ደረጃ ረቂቅ ህጉ የክልሉን አደረጃጀት ተከትሎ ከፌደራሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግ የተወሰደ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህንንም ህግ ለማዳበር በርካታ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን በማንሳት የዛሬውም የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ የበለጠ ሰነዱን ለማዳበርና ወደ ተግባር ለመቀየር ይረዳናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፉን ለማሳደግ እና የተሻለ ድጋፍና ክትትል ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የዜጎች የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግስታት በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በፌደራል ተቋማትና የክልል ባለድርሻ አካላት መካከል ገንቢ የሆኑ ግንኙነቶች መፈጠሩና ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋቱ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች ወደ ተሻለ ደረጃ እያደጉ መምጣታቸውንም አክለው ገልጸዋል ፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዘርፉ የተሻለ የአሰራር ስርዓት ለመፍጠር እና በህጎች ዙሪያ በሁሉም አስፈጻሚ አካላት ዘንድ እኩል ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል በአዋጁ እና በጸደቁ መመሪያዎች ላይ ለሁሉም ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መካሄዳቸውን እና ክልሎች የራሳቸውን ህግ እንዲያወጡ ድጋፍ የማድረግ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በሁሉም ክልሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መኖሩ በዘርፉ በፌዴራል ደረጃ የተገኘውን ምቹ ሁኔታ በክልሎች በተመሳሳይ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽ ያለው መሆኑን በማንሳት በአንድ ክልል ብቻ ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ቀላልና ምቹ የምዝገባ አስተዳደር ስርአት ለመፍጠር እንዲሁም በፌዴራል መንግስቱ ተመዝግበው ወደ ክልሉ ፕሮጀክት ለመፈጸም የሚመጡ ድርጅቶች ቀላል፣ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አሰራር ለመዘርጋት ይህ አዋጅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ክልሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለውይይት በማቅረቡ አመስግነው ባለስልጣን መስሪያቤቱ ከረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ጀምሮ የግብአት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረኮችን ድጋፍ እንዳደረገው ሁሉ ወደፊትም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመድረኩ በክልሉ የሚመለከታቸው የመንግስት አስፈጻሚ አካላት እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
read more