የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገር ልማት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና በሰላም ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተገለጸ፡፡

ይህ የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መድረክ ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለፋይናንስ ቢሮ እና በኦሮሚያ ክልል ለሚሰሩ የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች በፀደቁ 8 መመሪያዎች ላይ ስልጠና በሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አዋጅ 1113/2011 በተሟላ መልኩ ለማስፈጸም መመሪያዎችን ማውጣት እንዳለበት አዋጅ 1113/2011 ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሰረት አስራ ሰባት መመሪያዎችን በማዘጋጀት ስምንቱን መመሪያዎች በማጽደቅ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በአዳማ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገር ልማት፣ በዴሞክሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና በሰላም ግንባታ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በመግለጽ ክፍተቶችን የሚሞሉ ሳይሆኑ ስትራቴጂካዊ የልማት አጋር መሆናቸው በመንግስት ደረጃ መያዙን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ላለፉት አራት ዓመታት አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ከፌደራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመናበብ በርካታ የለውጥ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለውጡን ለማስቀጠል በአዲስ መንፈስ ሁለተኛውን የለውጥ ምዕራፍ አዲስ መዋቅር በመዘርጋት ወደስራ መግባቱን አብራርተዋል፡፡ ባለፉት አራት የለውጥ አመታት ወደኋለ የማይመለስ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና በዘርፉ ላይ መሰረት መጣሉንም አንስተው ህግ ብቻ ማውጣቱ ትርጉም ስለሌለው በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ህግን በሚገባ ተረድተው መተርጎም መቻል አለባቸው ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአሰራር ስርዓቱን የተሻለ ለማድረግ የተለያዩ ማንዋሎችን፣ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱንም ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ይህን ስልጠና ለመስጠት ድጋፍ ያደረጉ አካላትን በማመስገን ስልጠናው እስከ ታችኛው አካል ወርዶ በዞንና በወረዳ መስጠት እንዳለበትም ለተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡ በፀደቁ መመሪያዎች ላይ ስልጠና የሰጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የክትትል፣ ግመገማና ምርመራ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ ወርቁ እና የአገር በቀል ድርጅቶች የድጋፍና አገልግሎት ዴስክ ሀላፊ አቶ ዳንኤል ግዛው ናቸው፡፡