ተቋሙ ከአጠቃላይ ሰራተኛ ጋር በ2015 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የቀጣይ 6 ወራት የተከለሰ እቅድ ላይ እየገመገመ ይገኛል፡፡ በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መገምገም ከእቅድ አንጻር የደርስንበትን የአፈጻጸም ደረጃ ለማወቅና ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም መልካም አፈጻጸሞቻችንን አጠናክረን ለማስቀጠል ይጠቅመናል ብለዋል፡፡ በባለፉት የለውጥ ዓመታት የህግ እና ተቋማዊ ሪፎርም አንጻር መሰረት ተጥሏል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ እንደሃገር በርካታ ያለፍንባቸው ፈተናዎች ቢኖሩም በዛ ውስጥ አልፈን ዛሬ ለደረስንበት ከፍተኛ ውጤት በቅተናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛው የለውጥ ምዕራፍም የተገኙ ምቹ መደላድሎችን ውጤታማ እንዲሆን መስራት፣ከወረቀት ወደ ወረቀት አልባ አሰራር መቀየር እስካሁን ያገኘናቸውን ውጤቶች ማጽናት ላይ ትኩረት አድርገን መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የአንድ ተቋም ውጤታማነት የሚለካው በሚሰራው ስራ ብቻ ሳይሆን በሰራተኞቹ ስነ-ምግባር በመሆኑ ሁሉም ሰራተኛ በስነ-ምግባር የታነጸ፣እንደሰራዊት ለአንድ ዓላማ የሚሰራ እና እርስ በእርስ የሚደጋገፍ እንዲሆን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡