የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም፣ ሰብዓዊ መብቶች መከበርና መልካም አስተዳደር ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ዘንድሮም ለ3ኛ ጊዜ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ይከበራል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ካውንስል በጋራ 3ኛውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው መንግስት ዘርፉን ለማጠናከር ከተሰሩ ስራዎች አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንትን በማዘጋጀት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የርስ በርስ ትስስርና መስተጋብርን ለማጠናከር እንዲችሉ እንዲሁም ልምድ ልውውጥ ለማድረግ ትልቅ እድል የፈጠረ እንደሆነ የሲቪል ማህበረሰብ ድርርቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ገልጸዋል፡፡ መንግስት በርካታ የህግና ተቋማዊ ሪፎርም ካደረገባቸው ዘርፎች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የግሉንና የመንግስት ሴክተሩን በማስተሳሰር ሚዛናዊ ለማድረግና ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን ይችላሉ የሚል እምነት በመኖሩ ዘርፉን ለማጠናከር በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ ድርጅቶችን የመመዝገብና ድጋፋዊ ክትትል የማድረግ እንዲሁም የህግ ጥሰት ሲኖር የእርምት እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አንስተው በሚቀጥሉት አምስት አመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር አሁን ካለበት ወደ አስር ሺህ ለማድረስ እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ለሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉ ድምጽ ከመሆንና ዘርፉን ከማስተባበር ባለፈ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገሪቱ እያበረከቱ ያሉትን የማይተካ ሚና የማስተዋወቅና መድረኮችን በማመቻቸት በቂ ግንዛቤን የመፍጠር ኃላፊነት ያለበት መሆኑን አንስተው ሳምንቱ መከበሩ ድርጅቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸውን ትስስር አጠናክረው በጋራ መስራት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በግንቦት ወር ይከበራል ተብሎ በሚጠበቀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት አጋርነትን፣ ትስስርንና ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር ከልማት አጋሮች እና ከህዝቡ ጋር መስተጋብር መፍጠር፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን አስተዋጽዖ ለህዝብና ለሚመለከታቸው ባለስድርሻ አካላት ማሳየት፤ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል እና በሌሎች የልማት ተዋናዮች መካከል የልምድ ልውውጥን ማሳደግ እና በመንግስት፣ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና በግሉ ዘርፍ መካከል ለበለጠ ትብብር መድረክ መፍጠር ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፍላጎታቸውን ማሳወቅ እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን ስኬታም ሳምንት ለማሳለፍና ዘርፉ ይበልጥ ጎልቶ እንዲተዋወቅ በሚል ቅድመ ዝግጁቱ ከወዲሁ እንዲጀመር እንደተደረገ ተጠቁሟል፡፡