ተቋሙ ከጀስቲስ ፎር ኦል ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በውይይቱም በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች የተለያዩ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ሃላፊዎችና ተወካዬች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ የጀስቲስ ፎር ኦል መስራችና ፕረዘዳንት ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ እንዳሉት ድርጅቱ በፍትህ ስርዓት ውስጥ ለባለፉት 30 ዓመታት የሴቶች፣ የህጻናት እና የእስረኞች መብት ላይ በመስራት እና የህግ ዘርፉ በስርዓት እንዲመራ ለማስቻል የራሱን አሻራ አኑሯል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሴቶችና ህጻናት ላይ ብቻ ሳይሆን በሰላም ላይ መስራት አለብን ከዚህ አንጻር እዚህ ውይይት ላይ የተሳተፍን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሃገራችንን ሰላም ለማስጠበቅ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባደረጉት ንግግር የኢፌድሪ ህገ መንግስት ካረጋገጣቸው መብቶችንና ጥቅሞች መካከል አንደኛው ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው የሚደነግገው ክፍል አንዱ መሆኑን አንስተው ይህንኑ የህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች ተከትሎ መንግስት በሴቶችና በሕጻናት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያደርሱ የነበሩ ህጎችን በማሻሻል ተጨባጭ የድጋፍ እርምጃዎች በመውሰድ ሥር ሰድዶ የቆየውን ችግር ለማቃለል ብሎም የተዛቡ አመለካከቶችን ለማረም ከፍተኛ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈንና የሴቶችን ሁለንተናዊ ብቃት ለማረጋገጥ በርካታ እርምጃዎች የወሰደች ሲሆን እነዚህ እርምጃዎችም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ፤ ሴት ልጆች እንዲማሩ ጥረት ማድረግ፤ ሴቶችንና ሕጻናትን ከጥቃት መከላከል፤ ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነት ማምጣት፤ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሕጎችን በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ የሴቶችንና የሕጻናትን መብት ከማስከበር አኳያ አጽንኦት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሴቶችና ሕጻናትን ማዕከል ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ወደ ውጤት ለመቀየር ከመንግስትና ከግሉ ሴክተር ባልተናነሰ መልኩ መንግስተዊ ያልሆኑ ተቋማት በተለይም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጉልህ ሚና እንደላቸውም ይታመናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የሴቶችንና የሕጻናትን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የህጎች መሻሻል ብቻውን ውጤታማ ሊያደርገን ስለማይችል ሕጎች በጥብቅ ዲሲፒሊን እንዲመሩ የብዙ ተዋንያን ርብርብ ያስፈልጋል በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያለባቸው ከፍተኛ ኃላፊነት በመገንዘብ ውጤታማ ሴቶች ወደ ፊት በማምጣት፤ ለሴቶች መብት መከበር ማነቆ ወይም እንቅፋት የሆኑ በማህበሰረቡ ውስጥ ያሉ ስር የሰደዱ የተዛቡ አመለካከቶችን በማረም፤ የስርዓት ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የወንዶች ተሳትፎን በማበረታታት ረገድ የበኩላቸውን ሚና ሊጫወቱ ይገባል ሲሉ አብራርተዋል፡፡በመጨረሻም የሴቶችና የሕጻናት መብቶችን ለማስከበር የተቋቋሙ ድርጅቶች ጠንካራ ሕብረት በመመስረት በተበታተነ ሁኔታ የሚያካሄዱትን ትግል በተደራጀ፤ በተናበበና ተጽዕኖ ሊፈጥር በሚችል መልኩ መደራጀትና መንቀሳቀስ ያስፈልጋቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የሴቶች መብቶች፣ትግበራና ክፍተቶች በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ወ/ሮ አሸነፈች አበበ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ም/ፕረዝዳንት የጥናት ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል፡፡