የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የተቋሙ የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በጉብኝቱ ተሳትፈዋል፡፡ ጉብኝቱ የተደረገው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ፣ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በዎላይታ ሶዶ ዞን ሶዶ ከተማ እና ዳሞትሶሬ ወረዳ የሚገኙና ፒኤስ አይ ኢትዮጵያ (PSI Ethiopia) በቅንጅት በሚሰራባቸው ፕሮጀክቶች ነው፡፡ በጉብኝቱ የአፍላ ወጣቶችን እርግዝና ለመቀነስ በሻያንባ ቅሌና ቀበሌ ጤና ኬላ እየተሰራ ያለውን የብልህ ጅማሮ ፕሮግራም እንዲሁም የኤች አይ ስርጭትን ለመቀነስና በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን መደገፍና የምክር አገልግሎት መስጠትን ዓላማ ያደረገው የሙሉ ፕሮጀክት፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በተለይ በሀዋሳ ከተማ በሚሊኒየም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ትኩረት ያገኙ ናቸው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ከጉብኝቱ መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት አስተያየት በማህበረሰብ አቀፍ የጤና አጠባበቅ ላይ የተሻሻሉ የሽንት ቤት ሳኖፓትሪዎችን በማቅረብ የማህበረሰቡን የጤና አጠባበቅ ዘይቤ ለመቀየር እና ለወጣቶችም የስራ እድል ለመፍጠር የተሄደበትን ርቀት እንዲሁም በአፍላ እድሜያቸው በወሲብ ንግድ በተሰማሩ ሴቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የኤች አይቪ ምርመራና የምክር አገልግሎት እንዲሁም ለቫይረሱ የተጋላጭነት ደረጃ ለመቀነስ ድርጅቱ እያደረገ የሚገኘው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡
መንግስት የሲቪክ ምህዳሩ እንዲሰፋ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገር ልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ጉለህ ድርሻ እንዲኖራቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን ከመዘርጋት ባለፈ ድርጅቶች የሚሰሯቸውን ፕሮጀክቶች መስክ ድረስ ወርዶ በማየት ያለባቸውን ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በየደረጃው ከሚገኙ የመንግስት መዋቅሮች ጋር በትብብር መስራት መቻላቸው ውጤታማ እንደሚያደረጋቸው በዎላይታ ሶዶ ዞን የተሰሩ ስራዎች ትልቅ ማሳያ መሆናቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በትብብርና በቅንጅት መስራት ውጤታማ እና የተሻለ እንደሚያደርግ ጠቁመው በብልህ ጅማሬ በተለይ ሴቶች በአፍላ እድሜያቸው ለእርግዝና እንዳይጋለጡ ከማንቃት ባሻገር ወደትምህርታቸው እንዲመለሱ እንዲሁም በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ከወሲብ ንግድ ወጥተው ድርጅቱ በዘላቂነት ገቢ የሚያገኙበትን ዘዴ ቢመለከት የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ፡፡
የፒኤስ አይ ኢትዮጵያ population service International Ethiopia (PSI Ethiopia) የኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑት ዶክተር ዶሮቲ PSI Ethiopia የተለያዩ ስልጠናዎችንና ቴክኒካል ድጋፎችን በማድረግ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ አንስተው በህብረተሰብ ጤና፣ ስነተዋልዶ ጤና፣ የስራ እድል ፈጠራና የገበያ ትስስር ላይ የተለያዩ ስለልጠናዎችን በመስጠትና የቴክኒክ እገዛዎችን እንደሚያደርግ አንስተዋል፡፡ በጉብኝቱ እጅግ መደሰታቸውን የገለጹት ዶክተር ዶኸርቲ በጉብኝቱ ወቅት የተሰጡ ገንቢ አስተያየቶች ወደፊት በስፋት እንደሚሰሩባቸው ጠቁመው ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር ያላቸውንም ቅንጅት አጠናክረው በመቀጠል የህብረተሰቡን ችግር በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉ ስራዎችን ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ፒኤስ አይ ኢትዮጵያ population service International Ethiopia (PSI Ethiopia) በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2003 የተቋቋመና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን በስነ ተዋልዶ ጤና፣ በማህበረሰብ ጤና አጠጠባበቅ እንዲሁም ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ የሚሰራና መሰል ስራዎችን የሚደግፍ ነው፡፡ ሀዋሳ በሚገኘው ቢሮው በሲዳማ፣ እና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ብቻ ከ71 በላይ ወረዳዎችን በፕሮግራሞቹ የደረሰ ሲሆን በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡