የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ 1113/2011 የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት እና በተቋሙ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት በመፍጠር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ለመደገፍ፣ ለመከታተል ብሎም የህረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዛሬው ዕለት ተቋሙ ከCSSP2 ጋር በመተባበር በአካል ጉዳተኞች መብትና አካታችነት ላይ ለተቋሙ አመራሮች ለሁለት ቀናት የሚቆይ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ በስልጠናው ላይ የተገኙት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለአራት ዓመታት በለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑን በመጥቀስ በአሁን ጊዜ አዲስ የለውጥ ስሜት እና አዲስ አደረጃጀት መፍጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በተቋሙ አዲስ በተደራጀው መዋቅር ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን የሚከታተል ዴስክ መካተቱን አንስተው በርካታ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች በመኖራቸው እነዚህ ድርጅቶች የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በተሟላ መልኩ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሰራተኛውን አቅም ማጎልበት ቀዳሚ ተግባር ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በአካል ጉዳተኞች መብትና አካታችነት ላይ የተሰጠውን ስልጠና እንዲካሄድ ለተባበረው CSSP2 ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡