የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስጣንና የሲቪል ማህበረሰብ ድረጅቶች ምክር ቤት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ 4 ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በገንዘብ የተሰበሰበውን ድጋፍ ለተጎጂዎች ለማድረስ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ የተፈረመው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ጉዳት ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የተሰበሰበውን የገንዘብ ድጋፍ በቀጥታ ለማድረስ እንዲያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቸ ካውንስል በተናጠል ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ከተወሰኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ስምምነት በማድረግ የተሰበሰበው የገንዘብ ድጋፍ በቀጥታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ እምነት ያለን በመሆኑ ይህን ስምምነት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ 4 ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ሊደረግ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርቶች ምክር ቤት ጋር በመሆን ወደ 1 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ለተጎጂዎች ለማሰብሰብ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን አንስተው ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካሁን በፊት ሲያደርጉ እንደነበረው ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አድርገዋል፡፡
መንግስት ያደረገው ስምምነት መሬት ላይ ወርዶ ፍሬያማ እንዲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ማህበረሰቡ በሚያጋጥመው ማንኛውም ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊ ችግር ቀድሞ በመድረስ የመደገፍና የማገዝ የህግም ሆነ የሞራል ግዴታ ያለባቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ለማገዝ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተው በቅርቡ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ያቀፈ ኢኒሼቲቭ ለማቋቋም ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት እየሰራን እንገኛለን ያሉት አቶ ሄኖክ መለሰ ዛሬ የተደረገው ስምምነት ትልቅ ኃላፊነትን የሚሰጥና ለተጎጂዎችዎች በትክክል ለመድረስ የሚያግዝ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ስምምነቱ የተፈረመው ፋና አዲስ ትውልድ ኢትዮጵያ፣ ሪዲም ዘ ጀነሬሽን፣ ሴቭ ዩር ሆሊ ላንድ አሶየሽን እንዲሁም ተጋሩ ኢኒሼቲቭ ፎር ፒስ ኤንድ ሪሃብሊሽን ፎር ኢትዮጵያ ከተባሉ ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር ሲሆን በስምምነቱ መሰረት በጥሬ ገንዘብ የተሰበሰበው ድጋፍ በነዚህ አራት ድርጅቶች በኩል ለተጎጂዎች እንዲደርስ የሚያስችል ነው፡፡

ስምምነቱ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በመንግስት መካከል ትልቅ መተማመንን የሚፈጥር እንደሆነና የተጣለባቸውን አደራ በትክክል ለመወጣት ስምምነቱን የፈረሙት ድርጅቶች ተወካዮች የገለጹ ሲሆን በቀጣይም በርካታ ስራዎችን ተጎጂዎች ባሉበት አካባቢ ሁሉ ለመስራት ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ጠቁመዋል፡፡ በመርኃ ግብሩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ የቀረበ ሲሆን ለዚሁ ዓላማ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡