ለክልል ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዎችና ለባለስልጣን መስርያቤቱ የተለያዩ የስራ ክፍል ሃላፊዎች በፀደቁ አራት መመሪያዎች ላይ ስልጠና ተሰጠ፡፡ ከአራቱ መመሪያዎች በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በየክልሎቹ በመመሪያዎች ላይ የተሰጡ ስልጠናዎች በተመለከተ ግምገማ ተደርጓል፡፡ በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት አራት ዓመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ በተሻለ መልኩ ለመምራት ያስችል ዘንድ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እንደተሰሩ እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ምህዳር በተሻለ መልኩ ክፍት ለማድረግና ለሀገር ልማትና ዲሞክራሲ ግንባታ ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ እንዲሄድ ለማድረግ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል ፡፡ አዋጅ በሚወጣበት ወቅት ጥቅል ፖሊሲውን ይዞ ነው የሚወጣው አዋጁን ተከትሎ የሚወጡ ደንብና መመሪያዎች ደግሞ አዋጁን በደንብ ግልጽ ያደርጋሉ ብለዋል ፡፡ አያይዘውም ደንቡ በተለያዩ ምክንያቶች በተፈለገው ጊዜ አልወጣም ነገር ግን ደንቡ እስኪፀድቅ ድረስ በመጠባበበቅ ሴክተሩ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ተፅህኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ለባለስልጣን መስሪያቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት መመሪያዎችን በማውጣት ስራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል ፡፡ በመጨረሻም እነዚህ መመሪያዎች ለአገልግሎት ሰጪውም ሆነ አገልግሎት ለሚያገኘው ብልሹ አሰራርን ከመከላከል አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ መመሪያውን በተገቢው ተረድተን እና ተገንዝበን መጠቀም ይኖርብናል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡