የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽንን ከማርቀቅ ጀምሮ እሰከ ማፅደቅ በነበረው ሂደት ንቁ ተሳትፎ ስታደርግ መቆየቷ እና በኋላም በዓለምአቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ለሚገኘው የፀረ-ሙስና ትግል አጋርነቷን በማሳየት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በድህነት ውስጥ ባለች ሀገር “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ሙስናና ሌብነት የእድገታችን ማነቆ ሆኖ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያደረሰብን ይገኛል፡፡ በተለይም ሕዝብን ለማገልገል የተቋቋሙ አገልግሎት ሰጪ የሆኑ መንግስታዊ ተቋማት ከሌብነትና ብልሹ አሠራር በፀዳ መልኩ በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል ሲገባቸው ይህንን ኃላፊነታቸውን ለጊዜያዊ ጥቅም አሳልፈው በመሸጥ የሀገራችንን እድገት በእጅጉ ወደ ኋላ እየጎተቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በተቋማችን አገልግሎት ስንሰጥ ያስቀመጥናቸውን ተቋማዊ እሴቶቻችን ባከበረ መልኩ በአጋርነት እና በትብብር በመስራት፣ግልጽነት እና ተጠያቂነት፣በማስፈን ቅንነት እና ታማኝነት በመላበስ፤ፕሮፈሽናሊዝምን ባከበረ መልኩ እንዲሁም፣ምላሽ ሰጪነትንና ሰብአዊነት ማዕከል አድርገን ማገልገል የሚጠበቅብን ሲሆን እንደተቋም ሌብነትና ብልሹ አሰራርን በተመለከተ ዜሮ ቶለራንስ (zero-Tolerance) የሆነ መሪህን የምንከተል መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እወዳለሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት ክፉኛ መማረሩን አንስተው ለዚህ ደግሞ አፋጣኝ መፍትሔ ካልሰጠን መጨረሻው ትልቅ ቀውስና ትርምስ ይሆናል፤በመሆኑም መንግስት ይህንን ችግር ለመታገል ባለው ቁርጠኝነት በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ፀረ-ሙስና ኮሚቴ በማቋቋም ሌብነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመታገል መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ የተጀመረ መሆኑን አንስተው ሁሉም ዜጋ ተጨባጭ መረጃ በመስጠት ሌቦችን ማጋለጥና ለሕግ እንዲቀርቡ ለማድረግ በቁርጠኝነት መሥራት ይኖርብና ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ወ/ሮ ትግስት አቡዬ የስነምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው ስለበዓሉ ባስተላለፉት መልዕክት የዘንድሮው የጸረ ሙስና ቀን ‹‹ሙስናን መታገል በተግባር›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19 ግዜ በሃገራን ደግሞ ለ18ኛ ግዜ እየተከበረ መሆኑን በመግለጽ በሀገራችን ኢትዬጵያ በውስጥና በውጭ ጠላቶቿ የተከፈተባትን የሕልውና አደጋ በጽናት ተቋቁማ ወደብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ በሙስናና ብልሹ አሰራር ከቶውን እንዳይደናቀፍ በየደረጃው ከሚገኘው የመንግስት አመራና ሰራተኛ በተጨማሪ ከመላው ህብረተሰብ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በየዕርከኑ የምትገኙ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች ሙስና ውስብስብና አስቸጋሪ እንዲሁም የሚያደርሰውም ጉዳት ከፍተኛና ልዩ ባህሪ ያለው ወንጀል መሆኑን በመረዳ ከቃል ባለፈ ተግባራዊ ትግል ማድረግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የፕሮግራሙ ዓላማ፣ሀገራችን አለማቀፉ የፀረ-ሙስና ኮንቬንሽን አመሰራረት ታሪካዊ ዳራ፣የሙስና ምንነትና ትርጉም፣የሙስና ልዩ ባህሪያት፣የሙስና የህግ ማዕቀፎች፣በኢትየጵያ የጸረ-ሙስና ትግል እንቅስቃሴ፣የጸረ-ሙስና ትግል ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች፣የጸረ-ሙስና ትግል ቀጣይ አቅጣጫዎችና የባለድርሻ አካለት ሚና እንዲሁም ሌሎች ርዕሰ ጉዳዬችን ያካተተ ሰነድ አቅርበዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዓለማቀፍ የጸረ ሙስና ትግልን እና ጥናቶችን መሰረት ያደረገ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጥምረት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡