የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1113/11 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት የበጎ ፈቃደኝነትንና በጎ አድራጊነትን ባህል ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ስራዎች መካከል በጎ ፈቃደኞች ባሉበት ሆነው በፈለጉት የበጎ ፈቃድ ዘርፍ ላይ መሰማራት እንዲችሉ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው፡፡ በዚሁ መሰረት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ፈንድ አስተዳደር አማካኝነት ስራ ላይ የነበረው በጎ ፈቃደኞች ባሉበት ሆነው ለበጎፈቃድ አገልግሎት መመዝገብ እንዲችሉ የሚያግዝ የቮለንተሪዝም ኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ሲስተም (VIMS) ዘርግቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ይህን አሰራር በማዘመን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ዜጎችን የሚፈልጉ ተቋማት በቀጥታ ባሉበት ሆነው በጎ ፈቃደኞችን ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ሲስተሙ ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ ይህም ካሁን ቀደም ድርጅቶችና ተቋማት ጥሪ ተደርጎላቸው በደብዳቤ ጠይቀው ይወስዱበት የነበረው አሰራር ተቀይሮ በኦንላይን በፈለጉበት የሙያ ዘርፍ በጎ ፈቃደኞችን ማግኘት እንዲችሉ የሚያስችል ነው፡፡ የቮለንተሪዝም ኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ሲስተም በፕሪሚየም (volunteerism information management system) ደረጃ መበልጸጉን አስመልክቶ ከተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ የትውውቅና የግብዓት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት፤ በጎ ፋቃደኝነትን እንደሀገር ባህል ለማድረግ ሁሉም ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት አንስተው አሁን ተሻሽሎ በፕሪሚየም ደረጃ የቀረበው የቮለንተሪዝም ኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ሲስተም የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት ባህልን በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረጽ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የቮለንተሪዝም ኢንፎርሜሽን ማኔጅመንት ሲስተም ካሁን በፊት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት የሚፈልጉ በጎፈቃደኞችን በድህረ ገጽ የሚመዘግብ ሲስተም ሲሆን አሁን በተደረገለት ማሻሻያ ከበጎ ፈቃደኞች በተጨማሪ በጎ ፈቃደኛ ፈላጊ ድርጅቶችና ተቋማትም ተመዝግበው የፈለጉትን በጎ ፈቃደኛ ማግኘት እንዲችሉ የሚያስችል ነው፡፡