ጠቅላላ ጉባኤው ፕሮፌሰር ኢማና ጌቱን የጉባኤው ሰብሳቢ አድርጎ መርጧል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት በአገራችን የሙያ ማህበራት መቋቋም ረጅም ታሪክ ያለው ቢሆንም ለሙያ ማህበራት መደራጀት እና ማደግ ምቹ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ምክንያት ዘርፉ በማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ የሚገባውን ሚና እንዳይጫወት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በአገራችን በተካሄደው አገራዊ ሪፎርም ማግስት መንግስት ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ካሻሻላቸው ሕግች መካከል የሲቪል ማህበራትን የሚመራው ሕግ ሲሆን አዋጁ ያልተገደበ የዓላማ ነፃነት እንዲያገኙ ካደረጋቸው አደረጃጀቶች አንዱ የሙያ ማህበር መሆኑን አመላክተዋ፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ህግ ሙያ ማህበራት ለአባላት ጥቅም ካልሆነ በስተቀር ለሦስተኛ ወገን እንዳይሰሩ ተከልክለው የነበረው መሆኑን በመግለጽ በዚህም ሀገርና ህዝብ ከሙያ ማህበራት ማግኘት የሚገባውን ጠቀሜታ ሳያገኙ መቅረታቸውን አንስተዋል፡፡ አዋጁን ተከትሎ “የሙያ ማህበራት ድጋፍ እና አስተዳደር መመሪያ መውጣቱን አንስተው ባለሥልጣኑ በዘርፉ ከተሰማሩ የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር የሙያ ማህበራትን ለመደገፍና ለማበረታታት የተለያዩ ድጋፎችን ሊያመቻች እንደሚችልም በግልጽ መመላከቱን አብራርተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሙያ ማህበራት በተሻለ ሁኔታ ለመምራትና ለመደገፍ እንዲቻል በቅርቡ ተጠንቶ በጸደቀው አዲስ የባለሥልጣን መ/ቤታችን መዋቅራዊ አደረጃጀት አንድ ራሱን የቻለ “የሙያ ማህበራት ዴስክ” ያለው መሆኑን በማንሳት ይህ ዴስክ በቀጣይ ለሙያ ማህበራት የሚደረጉ ድጋፎችን በተደራጀና በተጠና መንገድ ለማከናወን እንደሚያግዝ ይታመናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በዛሬው ዕለት የሚመሠረተው የሙያ ማህበራት ህብረት (Ethiopian professional associations Alliance) ከዚህ በፊት በዘርፉ የነበሩትን ችግሮች በመቅረፍ የሙያ ማህበራት ተጠናክረውና ተደጋግፈው በችሎታና በዕውቀት የተገነቡ ተቋማት እንዲፈጠሩ፣የምርምር ስራዎች እንዲጎለብቱ በማድረግ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማስፋፋት አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ በማድረስ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና እንደምትጫወቱ መንግስት ከፍተኛ እምነት አለው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የጉባኤው መተዳደሪያ ደንብን ጨምሮ በርካታ መነሻ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በመጨረሻም ፕሮፌሰር ኢማና ጌቱ የጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ ፣አቶ ሰለሞን ደበሌ ም/ሰብሳቢ እና አቶ ሲሳይ ሳህሌ ጸሐፊ በማድረግ የመረጠ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ዘጠኝ አባላት ያሉት ስራ አስፈጻሚ አካላትን በመምረጥ ተጠናቋል፡፡