በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኢ.ፊ.ድ.ሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዋና ዳሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የትምህርት ቢሮ ሐላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ ተገኝተዋል። ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባስተላለፉት መልዕክት ADRA Ethiopia በትምህርት መሰረተ ልማት ግንባታ እያበረከተ ላለው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ አመስግነው ማህበረሰቡም ለተገነቡት ትምህርት ቤቶች ጥበቃ እና ደህንነት መስራት አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አድራ ኢትዮጵያ በትምህርት መሰረተ ልማት ግንባታ የትምህርትን ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት እና ጥራትን ለማስጠበቅ በመስራት በክልላቸው ውስጥ ቀዳሚ መሆኑን የገለጹት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ቶላ በሪሶ ድርጅቱ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል። የአድራ የፕሮግራም እና ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን አዋኖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የጀመረችውን ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተው የትምህርት ተደራሽነት ፣ፍትሐዊነት እና ጥራትን ለማሻሻል ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በእለቱም አምስት መቶ ሀምሳ ሺ ብር ወጪ የተደረገበት የምግብ ድጋፍ ለ50 አባወራዎች እና ቤተሰቦቻቸው የተደረገ ሲሆን ይህ ድጋፍ በቀጣይነት በዞኖቹ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የድርጅቱ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ብስራት አበራ አስታውቀዋል። የትምህርት መሰረተ ልማቶቹ ከኖርዌይ መንግስት እና ከ ADRA Norway በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መገንባታቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።