በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩበት የበጎ አድራጎት ድርቶችና ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 ሙሉ በሙሉ ተሽሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ 3 አመታት የተቆጠሩ ሲሆን አዲሱ አዋጅ በስራ ላይ መዋሉን ተከትሎ ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃት እየታየበት ይገኛል፡፡
የአዋጁ ተፈጻሚነት በፌደራል ደረጃ በተመዘገቡና በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ላይ ብቻ በመሆኑ በአንድ ክልል ብቻ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በፌዴራል ደረጃ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠርላቸው ቆይቷል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በክልሎች የመደራጀት መብትን ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ በፌዴራል ደረጃ ከወጣው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ህግ በክልሎች እንዲኖር ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ሁሉም ክልሎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህንን ረቂቅ አዋጅ ካዘጋጁት ክልሎች መካከል የሀረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህ ቢሮ እና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮዎች ከባለስልጣኑ ጋር በመተባበር ከዛሬ ጀምሮ ለ2 ቀናት ውይይቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

በሀረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሀረር ከተማ እተካሄደ በሚገኘው የውይይት መርኃ ግብር ላይ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ም/ቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱልባሲጥ አቡበከር እንዳሉት በፌደራልና በክልል ያለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግ ወጥነት ያለው መሆን አለበት በሚል መርህ የዜጎችን የመደራጀት መብት በክልሎች በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ምስጋናው በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቀደም ባለው የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ 621/2001 በርካታ ክልከላዎች የነበሩበት እንደነበረ አንስተው በፌደራል ደረጃ በአዲሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 እነዚህ ክልከላዎች ሙሉ በሙሉ ተነስተው የዜጎችን የመደራጀት መብት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የፌደራሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ እስከ ክልል ባለው መዋቅር ወጥነት ያለው ህግ እንዲኖርና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግን ተከትለው በየትኛውም ክልል ተንቀሳቅሰው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይችሉ ዘንድ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ የክልሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ራህመቶ እንደገለጹት ከሆነ በሀረሪ ብሄራዊ ክልል ውስጥ 32 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን ከ520 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ 36 ፕሮጀክቶችን ከክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ጋር ተፈራርመው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ክልሎች የራሳቸውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግ እንዲያዘጋጁ ሞዴል ረቂቅ ህግ ከማዘጋጀት ጀምሮ በርካታ የሙያና የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በሀረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባና አስተዳደር ረቂቅ መመሪያ ላይ የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ከክልሉ ፍትህ ቢሮና ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመሆን ግብዓት በማሰባሰብ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ሶስት ክልሎች የራሳቸውን የክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግ በየምክር ቤቶቻቸው ማጽደቃቸው ተገልጿል፡፡