የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከአውሮፓ ህብረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ (EUCSF III) እና ከብሪቲሽ ሲቪል ሶሳይቲ ሰፖርት ፕሮግራም (CSSP II) ጋር በመሆን ያስጠናው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በአዲስ አበባ ይፋ ተደርጓል፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ ሪፖርት ይፋ ሲደረግ የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስን ጨምሮ የተለያዩ ሚንስትሮችና የባለስልጣን መስሪያቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የዳሰሳ ጥናት ይፋ ሲደረግ እንዳሉት ጥናቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቀደም ሲል ከነበረባቸው ማነቆ ተላቀው አሁን ላይ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር መቻላቸውን አንስተው በተለይም አዲሱ አዋጅ ከወጣ በኋላ ከ2200 በላይ አዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስር ተመዝገበው መንቀሳቀስ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ታሪክ 50 ዓመታትን ወደኋላ ያስቆጠረ እንደሆነ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ አሁን ላይ መንግስት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግበው ለሀገር፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም ለህብረተሰብ ተጠቃሚነት የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ ለሪፖርቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱትን የጥናት ቡድኑ አባላትን እንዲሁም ለጥናቱ መሳካት አስተዋጽዖ ያበረከቱ አካላትን ሁሉ ዋና ዳይሬክተሩ አመስግነዋል፡፡ በመርኃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የዳሰሳ ጥናትን የተመለከተ አጭር ገለጻ በጥናት ቡድኑ መሪ አቶ ደበበ ኃይለ ገብርኤል የቀረበ ሲሆን የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እንዲሁም የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ደዔታ አቶ ታዬ ደንደዓና ጥሪ የተደረገላቸው ሚንስትር ደኤታዎች በጋራ የጥናት ሪፖርቱን ይፋ አድርገዋል፡፡