የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በንግግራቸው በአንድ ሀገር እድገትም ሆነ ውድቀት ውስጥ ሚዲያ ያለውን ሚና ማሳነሰ አይቻልም፡፡ በተለይም ዲጂታላይዝድ እየሆነ በመጣው ዓለም ውስጥ የሚዲያ ሚና በእጅጉ ጎልቶ እንደሚታይ እና አንዳንዴ ከተጽዕኖ ፈጣሪነቱና የሰዎችን አመለካከት ከመቅረጽ አኳያ እንደ 4ኛ መንግስትም ይቆጠራል ሲሉ ገልጸዋል ፡፡ አክለውም የሚዲያው ዘርፍ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም ከለውጡ በኋላ በሚዲያና በሲ/ማ/ድርጅቶች ዘርፍ የተከናወኑ የሪፎርም ተግባራት በተለይም የሕግና የተቋማዊ ሪፎሞች ሥራዎች በዘርፉ ይታይ የነበሩትን ህጸጾች በማረም አስቻይ ማዕቀፎች እንዲፈጠሩ መደረጉን በንግግራቸው ወቅት አስታውሰዋል፡፡ በቀጣይም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ ሙስናንና ብልሹ አሰራሮችን ከመዋጋት አኳያ ሚዲያና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ይጠበቃል ብለዋል ፡፡
የጋዜጠኝነት ሙያ እንዲሻሻል፣ በዘርፉ ያሉ ሙያተኞች ዕውቀታቸውን እንዲጎለብት፣ ብስለትና ሥነ ምግባር ያላቸው ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ፤ ለሰው ልጆች ክብርና መብት የሚሟገቱ ሀቀኛ ባለሙያዎች እንዲበዙና እንዲበረክቱ ከማድረግ አኳያ ዛሬ ምስረታው እውን የሚሆነው ማህበር አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በተለይም በአገራችን ካጋጠመን የእርስ በርስ ግጭት መነሻ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ በመግባት በተለያየ መንገድ የአሸባሪ ቡድኖችን በመደገፍ ሀገራችንን ለማፈራረስ ብሎም የሚሰጣቸውን የተሳሳተና የውሸት ትርክቶች በማራገብ የዓለም ማህበረሰብን ለማሳሳት የተሄደበት ርቀት ቀላል ባለመሆኑ ሚዲያዎች ሀቁን ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅ ላይ በቂ ስራ መሥራት ላይ አሁንም ከፊታችሁ ረጅም ጉዞ ይጠብቃችኋል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡