ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከተቋሙ ሰራተኞች በሰባት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር እያከናወነ ይገኛል፡፡ በግብዓት ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሩ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው የስራ ክፍል ሃላፊዎች፣ተወካዮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት አገልግሎት አሰጣጡን ግልጽ እና ተገማች እንዲሆን ለማስቻል 17 ረቂቅ መመሪያዎችን ያዘጋጀ መሆኑን በመጥቀስ ከአሁን በፊት ከጸደቁትና በተግባር ላይ ከዋሉ መመሪያዎች በተጨማሪ ሰባት ረቂቅ መመሪያዎች ለውይይት የቀረቡ መሆኑን አንስተው የተቋሙ ባለሙያዎች እንዲወያዩበትና አስተያየት እንዲሰጡበት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ለውይይት የቀረቡት 7ቱ መመሪያዎች የሲ.ማ.ድ ከታክስና ቀረጥ ነጻ አጠቃቀም ረቂቅ መመሪያ፣ በሲማድ ውስጥ ስለሚሰሩ የውጪ አገር ዜጎች የስራ ፈቃድ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያ፣ ስለውጪ ድርጅቶች ምዝገባና አስተዳደር የወጣ ረቂቅ መመሪያ ፣ እምነትን መሰረት ያደረጉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ስለመመዝገብና ለማስተዳደር የወጣ ረቂቅ መመሪያ፣ ህብረቶችንና ካውንስሎችን ለመመዝገብና ለማስተዳደር የወጣ ረቂቅ መመሪያዎች ሲሆኑ ከእነዚህ መመሪያዎች በተጨማሪ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ቦርድ የሚመለከት እንዲሁም የህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ለበጎ አድራጎት ተግባር ማዋልን የሚከለክሉ ናቸው፡፡