በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃደኝነት ቀንን ምክንያት በማድረግ የደም ልገሳ መርኃ ግብር ተከናውኗል፡፡ በደም ልገሳ መርኃ ግብሩ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የተቋሙ ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በደም ልገሳ መርኃ ግብሩ ወቅት ያነጋገርናቸው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በማህበረሰቡ ውስጥ የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት ባህል እንዲያድግ በአዋጅ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተሰጥቷል ያሉ ሲሆን ይህንንም ለመወጣት የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ ከነዚህም አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ማበረታታትና ማገዝ አንዱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደተቋም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ ተሳትፎ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር ለመወጣት ካሁን በፊት ያልነበረ አዲስ ልምምድ ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ስለተግባባን የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነትን ባህል ለማድረግ ራሱን የቻለ የስራ ክፍል በማቋቋም ወደ ስራ ገብተናል፡፡ በዚህ የስራ ክፍል አማካኝነት በአዋጅ የተሰጠንን ስልጣንና ኃላፊነት መሬት ላይ በማውረድ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተሰርቷል በማት አብራርተዋል፡፡ የበጎ ፈቃደኝነትን ለማጎልበትና ለመምራት የሚያስችል ጋይዳንስ ኖት ተዘጋጅቶ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ለሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የማስተዋወቅና ስልጠናዎችን መሰጠታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ጋር በመሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጎ ፈቃድ ፖሊሲ እንዲወጣ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በበጎ ፈቃደኝነት ላይ እንዲሳተፉ እና ሌሎችንም እንዲያሳትፉ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተሰርቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ማበረታታት፣ ስልጠናዎችን መስጠት፣ አቅማቸውን ማጎልበት በስፋት የሰራንበት ነው፡፡ ይህን ለማገዝ VIMS የሚባል ሶፍትዌር በማበልጸግ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ማንኛውም ግለሰብ ባለበት ሆኖ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መመዝገብ የሚችልበት አሰራር ከአንድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመሆን ሰርተናል፡፡ እንደሀገር ለበጎ ፈቃደኝነት ትልቅ ትኩት ተሰጥቷል፡፡ወደፊት የበጎ ፋቃድ ፖሊሲ ሲወጣ የበለጠ የሚዳብር እንደሚሆን ትልቅ እምነት አለን፡፡ የዛሬውን የበጎ ፈቃደኝነት ቀንን ስናከብር ግን በጎ ፈቃደኝነት አንዱ የህይወታችን አካል እንደሆነ ማሰብ እና አንዳችን ላንዳችን እጅግ አስፈላጊ እንደሆንን፤ ሰላምን እንደሚያሰፍን፣ ጠብን እንደሚያርቅ ታሳቢ የምናደርግበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ የተቋማችን ሰራተኞች ደም ሲለግሱ በሰጡት ደም የዜጎችን ህይወት እየታደጉ ያሉት፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በሚመለከት ግን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በፈቃደኝነት የሚመሰረቱና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ከመሆናቸውም በላይ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በጎ ፈቃደኝነትንና በጎ አድራጊነትን የስራቸው መሰረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ከሌላው ለየት የሚያደርጋቸውም የበጎ ፈቃደኝነት እሳቤን በመያዛቸው ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህን እሳቤያቸውን መሰረት አድርገው ወደፊትም መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው መልዕክቴን ላስተላልፍ እወዳለሁ ብለዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን ተከትሎ ከበጎ ፈቃደኞች ብዙ እንደሚጠበቅ አንስተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረውና ባህል እንዲሆን በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ በርካታ የበጎ ፈቃድ ተግባራት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተከናውነዋል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ተግባር ላለፉት ጊዚያት ሲወጡ ለነበሩ ድርጅቶችና ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ዜጎቻችንን ለመደገፍ ከመደበኛው ወቅት በበለጠ እያንዳንዱ ዜጋ በበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ መሳተፍና ዜጎቻችንን መደገፍ ይኖርበታል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ዛሬ እለቱን በማስመልከት የደም ልገሳ መርኃ ግብር ላይ የተሳተፉትን እያመሰገንን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት ተግባርን መርተውት ባህል እንዲያደርጉት በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡