የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከለውጡ በኋላ ያከናወኗቸው በርካታ አመርቂ ስራዎችን ለማስቀጠል ፣ ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየትና መፍትሄ በመስጠት የዳበረ የነቃና ሃላፊነቱን የሚወጣ ዘርፍ እንዲሆን ለማስቻል መድረኩ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ ዶ/ር ዓለሙ ስሜ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት እንደሃገር አራት ቁልፍ ሚና አላቸው ተብለው ከተለዩት ዘርፎች መካከል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አንድ መሆኑን በመግለጽ ይህንን የተገነዘበ እና ተመሳሳይ ምልከታ ያለው መዋቅር መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ሃገርን ለማሻገር የሁሉም ተዋንያን ተሳትፎ ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ ድርጅቶች የሰሯቸው በርካታ ተግባራት አበረታች ቢሆንም በዘርፉ ካለው እውቀትና ገንዘብ አንጻር ከዚህ የበለጠ መስራት ይጠይቃል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተዘራውን ጥላቻና ቂም በቀል አስወግዶ በሃገሪቱ ሰላምን ለማስፈን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ አቅምን አሟጦ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ጋር በቀጣይነት ያጋጠሙ ችግሮችን እየፈቱ ለመሄድ ተከታታይ የሆነ መድረኮች ማዘጋጀት፣በጋራ ማቀድና መስራት እንዲሁም መረጃ መለዋወጥ ያፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከለውጡ በኋላ በዘርፉ የተገኘ ስኬት፣ተግዳሮቶችና የቀጣይ አካሄዶች ላይ መነሻ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በቀረበው ሰነድ ላይም በርካታ ገንቢ ሃሳቦች፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በውይይቱ የፌደራል እና የሁሉም ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሃፊዎችና ተወካዬች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡