በፕሮግራሙ የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣የደቡብ ክልል ቢሮ አመራሮችና ሰራተኞች፣የከተማዋ ከንቲባ እና ነዋሪዎች ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ፕሮግራሙን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ እንዳሉት የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ከለውጡ በኃላ በመንግሥትና በግል ባለሃብቱ የማይሸፈኑ የልማት ሥራዎችን በመተካት ወሳኝ ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸው ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንደጸረ ሰላምና ሰላይ የሚታዩበት ሁኔታ አሁን ተቀይሮ ከመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብርና በጋራ ሀገር የማልማት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሀገር የምትበለፅገው አቅምና የተፈጥሮ ሃብትን አስተባብሮ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል መሆኑን ጠቁመው መርሐ ግብሩ አየር ንብረትን ለመጠበቅ ዛፍ ከመትከል ባሻገር አብሮነትንና ወንድማማችነትን በማጠናከር ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ እንድንተዋወቅ እድል የፈጠረ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ አክለው ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 4ኛውን የአረንጓዴ አሻራ የማሳረፍ አገራዊ ጥሪ መሰረት በማድረግ በዛሬው እለት በቡታጅራ ከተማ ችግኝ ለመትከል መሰባሰባቸው ዘርፉ በአገር የልማት እንቅስቃሴ ላይ በንቃትና ትርጉም ባለው መልኩ እየተሳተፈ የመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በባለፉት አራት ክረምቶች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች የአረንጓዴ ልማት ውጤታማ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜት የሚኖረው ከመሆኑ ባሻገር ለመጪው ትውልድ ለምለም ምድር የማስተላለፍ ሃላፊነት የሚሰማው ዜጋ የሚያከናውነው መልካም ተግባር ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ይህንን በመገንዘብ በችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ የምትሳታፉ ሁሉ አረንጓዴ አሻራ የሚያሳርፈው ትውልድ አካል ስለሆናችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያቤቱም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሮች ላይ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ተሳትፎ ማድረጉን እና በዘንድሮው መርሃ-ግብርም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመንቀሳቀስ አሻራ ማሳረፍ መቻሉን አንስተዋል፡ በመጨረሻም የችግኝ መትከል ፕሮግራሙን ከአዲስ አበባ ራቅ ያሉ የክልል ከተሞች በመንቀሳቀስ ማከናዎን መቻሉ ከችግኙ ከሚገኘው ጠቀሜታ ባሻገር የአንድነት፣የአጋርነት፣ የመተሳሳብ፣ የአብሮነት፣ የትብብር እና የወንድማማችነት እሴትን በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን በማንሳት ይህንኑ በጋራና በመቀናጀት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎት የሚደረገው የችግኝ ተከላ ዘመቻ ውጤታማ በሆነ መልኩ ሊቀጥል ይገባዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡