የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮች፣ የሲማድ ምክር ቤት ኃላፊዎችና ሰራተኞች የአመራር ክህሎትና አቅምን ለመገንባት ዓላማ አድርጎ የተቋቋመውን “የአፍሪካ የአመራር ልህቀት ማዕከልን በአካል ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡ ይህ ጉብኝት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በማዕከሉ ተጠቃሚ በመሆን በዘርፉ የአመራር አቅምን የበለጠ ማጎልበትን ታሳቢ በማድረግ በባለስልጣን መ/ቤቱ የተጀመረው ግንኙነት ቀጣይ አካል መሆኑ ተብራርቷል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት ከማእከሉ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ህይወት አለማየሁ ጋርም በቀጣይ በየሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማእከሉ መጠቀም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ በሱሉልታ ከተማ የሚገኘው ይህ ማዕከል ከ600 በላይ ተሳታፊዎችን በአንድ ጊዜ የመያዝ አቅም ያለው እንዲሁም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን በጠበቁ የስብሳባ አዳራሾችና ሌሎች ግብዓቶች የተሟላ ሲሆን የመንግስት፣ የሲቪል ማህበራትንና የግሉን ሴክተር የአመራር አቅም ለመገንባት የሚንቀሳቀስ መሆኑ በባለስልጣኑ ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 484/2013 ተደንግጓል፡፡ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ማዕከሉ ደረጃው በጠበቀ መንገድ አገልግሎት የሚሰጥ የአመራር አቅም ግንባታ ማዕከል መሆኑን በመግለፅ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአመራር ክህሎትና ብቃት በመገንባት በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው በመናገር ባለስልጣን መ/ቤቱም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማእከሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አመራሮች በበኩላቸው ማእከሉ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ የተገነባ መሆኑን አድንቀው የሲቪል ማህበራትን የአመራር ብቃት ለመገንባት እንደሲቪል ማህበራት በጋራ እንዲሁም በተናጥል በየድርጅቱ በማእከሉ ለመጠቀም ፍላጎት ያለ መሆኑን በመግለጽ ትብብሩ ስትራቴጅያዊ ሆኖ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ተገቢውን ተግባራት የሚያከናውን መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የማእከሉ ምክትል ርዕሰ አካዳሚ ወ/ሮ ሕይወት አለማየሁ እንደገለጹት ማዕከሉ ለመንግስት፣ ለሲቪል ማህበራትና ለግሉ ዘርፍ የአመራር አቅም ግንባታ አስተዋፅኦ ለማድረግ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ እና በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም በማእከሉ በመገኘት የአመራር አቅማቸውን ሊያዳብር የሚችሉ ስልጠናዎችን መውሰድ የሚችሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ከሲቪል ማህበራት ፍላጎት የሚነሳ የስልጠና ሞጁል የማዘጋጀት እቅድ ያላቸው መሆኑን አንስተው በዓለም አቀፍ እንዲሁም በአፍሪካ ደረጃ ላሉ የሲቪል ማህበራትም ማዕከሉ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን መስጠት የሚያስችል በግብዓትም ሆነ በይዘት ደረጃ የተደራጀ አቅም ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በውይይቱም በቅርቡ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮች በሚገኙበት የአመራር ወርክሾፕ በማእከሉ ለማካሄድ እንዲሁም ትብብሩን ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ የጋራ መግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡