ይህ የተባለው ለመስሪያ ቤቱ የማኔጅመንት አባላት እና ለሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች በፋይናንስ፣ኦዲትና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ባለበት ወቅት ነው፡፡ የፌደራል መንግስት የሂሳብ አሰራር ስርዓት፣የኢትዬጵያ መንግስት የሂሳብ ስርዓቶችን፣ሂሳብ ሪፖርት አዘገጃጀት፣የግዢና ክፍያ ስርዓት፣ የፋይናንስ ኃላፊነት እና አተገባበር ዙሪያ ከገንዘብ ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹ ተቋሙ የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶችን በመከታተልና በመቆጣጠር ብሎም የበጎ አድራጊነትና በጎ ፍቃደኝነት ባህልን ከማጎልበት አንጻር ከፍተኛ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አንስተው በዚሁ ልክ የውስጥ አገልግሎቶችን በማዘመን እና የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት ማሻሻያዎች ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የስልጠናው ዓላማ የባለበጀት መስሪያቤት እንደመሆናችን መጠን በእውቀት ላይ የተመሰረተ የሃብት አስተዳደር እና ውሳኔ ሰጪ እንድንሆን ብሎም ያለንን ውስን የፋይናንስ እና የንብረት ሃብት በአግባቡ በማቀድ መፈጸም እንዲያስችለን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡: በመጨረሻም ም/ዋና ዳይሬክተሩ ባስተላለፉት መልዕክት በዚህ ስልጠና ላይ የተሳተፍነው በቀጥታ በሃብት ላይ የምንወስን እና የምንመራ ሃላፊዎች እንደመሆናችን መጠን ከስልጠናው በኋላ ለውስጥ አገልግሎቶች ትኩረት በመስጠት፣ ከፋይናንስ አንጻር የተፈጠሩ የፋይናንስ አስተዳድር ውስንነቶችን በመፍታት፣እንደመንግስት ያለንንን ውስን ሃብት በእቅድ ላይ ተመስርቶ በመተግበር እና ለፈጻሚዎች በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ በማድረግ መስራት ይጠበቃል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡