በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስተባባሪነት በአገራችን በተከሰተው ጦርነት እና በድርቅ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ተሳትፎ ላደረጉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም አያካሄደ ይገኛል፡፡ በእውቅና ፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ እንደተናገሩት ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በዘለቀው ጦርነት ዜጎቻችን የመጎሳቆል እና መሰረት ልማቶች መውደማቸውን በማውሳት በተለይ በአማራ፣በአፋር እና በትግራይ ክልሎች በጦርነቱ እጅግ መጎዳታቸውን ገልፀዋል፡፡አያይዘውም ጦርነቱን ያነሳው የትግራይ ክልል አስተዳድራለው ያለው ድርጅት በዋነኝነት እወክለዋለው ያለውን ህዝብ ያጎሳቆለ መሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ጦርነቱ በነበረባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ያለአግባብ የሞቱበት፣የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ዜጎች የአስገድዶ መደፈር የደረሰባቸው፣ የስነልቦና ውድቀት የደረሰባቸው መሆኑን ሚኒስትር ዴታው አክለው ገልፀዋል፡፡
ሌላው ያነሱት በአንዳንድ የአገራች ክልሎች በተከሰተው ድርቅ የሰው ህይወትና በእንሰሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ያወሱተ ሚኒስትር ዴኤታው ጋን በጠጠር ይደገፋል እንደሚባለው ሁላችንም የአቅማችንን ያህል ለዜጎቻችን ድጋፍ በማድረጋችን ለምስጋና መብቃታችን የሚያኮራ ቢሆንም የደረሰው ጉዳት በአንድ ጊዜ የሚመለስ ሳይሆን ተከታታይ ድጋፎች እንደሚያስፈልግ አብራተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው በጦርነቱ ምክንያት በአማራና በአፋር ክልሎች በርካታ ወገኖቻችን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ የብዙ ንፁሀን ህይወት ተቀጥፏል፣ በርካታ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል እንዲሁም የማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ደርሷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የደረሱትን ጉዳቶች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያደረገው ጥሪ በመቀበል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እስካሁን 430 ሚሊየን ብር በዓይነትና በገንዘብ መሰብሰቡን በመግለጽ 413 ሚሊዮን በዓይነት ሲሆን 17 ሚለዮን ብር በጥሬ በቀጥታ ለተጎጂዎች መድረሱን አብራርተዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያቸያን በርካታ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን አንድ ሆነን እንደተሻገርን ዛሬም ትልቅ ሀላፊነት ለመወጣት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሳዩት ርብርብ ዋና ዳይሬክተሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ሌላው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ለጥፋት የተዘጋጁ እጆች እንዳሉ ሁሉ ለበጎ ሰራ የተዘረጉና ሁሌም የሰው ልጅ ጉዳት የሚከነክናቸውና የቻሉትን ያህል ለበጎነት የሚዘረጉ እጆች መኖራቸው ተስፋ ይሰጣሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አገራችን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ብታልፍም ፈተናዎቹ ቢያጠነክሯት ቢሆን እንጂ ሊያጠፋት እንደማይችሉ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡ የተደረገውን ድጋፉ በተመለከተ አጠቃላይ ሪፖርት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር በአቶ ፋሲካው ሞላ ቀርቧል፡፡ የሶማሌ፣ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች አሁን ያለውን የክልላቸውን ተጨባጭ ችግሮች ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡