በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት የመደራጀት መብት የሌሎችን የሰው ልጅ መብቶች ከማክበርና ማስከበር እንዲሁም ተግባራዊ እንዲሆኑ ከማስቻል አንፃር የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚጫወት ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስትም ይህን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት ዜጎች ለተለያዩ ዓላማዎች በመደራጀት የራሳቸው እና የሌሎች ሰዎችን መብቶች ይበልጥ እንዲከበሩ ለማድረግ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ማቋቋም የሚችሉበት የሕግ ስርዓት ተበጅቶ ሲተገበር መቆየቱን አንስተዋል፡፡ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 ዘርፉ በሚፈለገውና በሚገባዉ መጠን እንዳይንቀሳቀስ የገደበ ፣ ለመደራጀት መብት ትልቅ ፈተና የነበረ ፤ በተለይም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የገቢ ምንጭ እና ከሚሰማሩባቸው የሥራ መስኮች አንጻር ከፍተኛ ገደብ አስቀምጦ እንደነበር ገልጸው አዲስ የወጣዉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በርከት ያሉ ፋይዳዎች ያሏቸው ጉዳዮችን ከማካተቱም ባሻገር ቀደም ሲል የነበሩ ገደቦችን ሙሉ በሙሉ በማንሳትና የዜጎችን በነጻነት የመደራጀት ምህዳር በማስፋት ማናቸውም ድርጅት ሕጋዊ ለሆነ እና ዓላማው ለትርፍ ላልሆነ ማንኛውም ዓይነት ሀገርንና ሕዝብን ይጠቅማል ብሎ በሚያስባቸው ጉዳዮች ላይ መሰማራት እንዲችል የሚፈቅድ ሆኖ እንደተሻሻለ እና ይህም መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ ቁርጠኛ አቋም መዉሰዱን ያሳየበት የመጀመሪያዉ እርምጃ ነዉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ እና መሰል ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም የዜጎችን የመደራጀት መብት በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ ፣ ከዘርፉ ሕዝብና መንግስት ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅም በአግባቡ ለማግኘት እንዲሁም ድርጅቶች ሊያደርጉ የሚችሉትን አስተዋፅኦ በሚገባ አሟጦ ለመጠቀም እንዲቻል ጉዳዩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግስታት የበለጠ ተጠናክረው ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለልማትና ዲሞክራሲ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ እንዳለ ሆኖ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ የሕብረተሰብ ተጠቃሚነትን እና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ አግባብ መሆኑን እንዲሁም በሕዝብ ስም የሚመጣ ሀብት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሌላው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባስተላለፉት መልዕክት አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ፀድቆ ተግባራዊ ከሆነ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው ከ1800 በላይ የውጭና ሀገር በቀል ድርጅቶች በፌዴራል ደረጃ ተመዝግበው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን በክልል ደረጃም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ድርጅቶች መመዝገባቸውን ለማረጋገጥ ችለናል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በሀገራችን የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን በማድረግ ውስጥ ይህ ዘርፍ ተሳትፎው ከግዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመምጣቱም በተጨማሪ፣ በመንግስት በኩል ያጋጠሙን የሀገራችን የሠላም እጦት በምክክር ለመፍታት የተጀመረውን ጥረት የኮሚሽኑን አባላት ብቃት ያላቸው ገለልተኛ ሰዎች እንዲመረጡ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል፤አሁንም የኮሚሽኑ አባላት ስራ ስኬታማ እንዲሆን ህዝቡ በራሱ ጉዳይ ላይ በያገባኛል ስሜት መሳተፍ እንዲችል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በጉባኤው ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዬች በክልል ደረጃ የሲቪል ማኅበራትን ለመከታተል የተመደቡ ( CSO Desk) የስራ ኃላፊዎች የተወያዩበትን ተሞክሮ፣ በተቋማችን የተጀመረውን የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ እንዲሁም በባለሥልጣን መስሪያቤቱ የተዘጋጀውን የክትትልና ግምገማ ማኑዋል ይዘት ዝርዝር ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ሌላው በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተከሰተው ችግር ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል 6 ሚሊየን ብር ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ተቋሙ ለክልሉ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም የሁልግዜ ተባባሪ ለሆነው CSSP 2 ምስጋናቸውን አቅርበዋል