የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በተቋሙ ለሚገኙ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ባለሙያዎች ትኩረቱን በፋይናንስ አሰራር ስርዓትና በንብረት አያያዝ ላይ ያደረገ ስልጠና ከፕላን ኢንተርናሽናል ጋር በመተባበር ከገንዘብ ሚንስቴር በመጡ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው ወጪ ቆጣቢ የኃብት አጠቃቀምን በማሳደግ ዓላማችንን ማሳካት ይጠበቅብናል ያሉ ሲሆን የሂሳብ አያያዝ ስርዓታችንን በማዘመን ስራዎቻችንን መከወን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡አያይዘውም በእውቀት ላይ የተመሰረተ አፈጻጸምን ለማጎልበት ስልጠናው እጅግ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ስልጠናውን እንድንሰጥ ላገዙን ሁሉ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ብለዋል፡፡ በፋይናንስ የሪፖርት ስርዓታችን ላይ ማሻሻል የሚገቡን በርካታ ስራዎች ያሉን በመሆኑ ተሳታፊዎች በትጋት እንድትከታተሉ ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ከገንዘብ ሚንስቴር በመጡት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መኮንን ጌታሁንና ወ/ሮ ተናኘ ጌታሁን አማካኝነት ስልጠናው ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የተቋሙ የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ባለሙያዎች፣ የውስጥ ኦዲት ባለሙያዎችና የተቋሙ ንብረት ክፍል ባለሙያዎች የስልጠናው ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡ ስልጠናው በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው የመንግስት ሂሳብ አያያዝ፣ የጥሬ ገንዘብ አስተዳደርና ቁጥጥር በእጅ ያለ ጥሬ ገንዘብ፤ በባንክ ያለ፣ ተሰብሳቢ ሂሳብ፣የወጪ አስተዳደር፣ ደመወዝና አበል ክፍያ፣ግዥ፣ ንብረት አስተዳደር፣ ስጋት እና የስጋት አስተዳደር ፣ በሚሉ መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

ከስልጠናው መጠናቀቅ በኋላ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን የሰጡ ሲሆን በስራ ላይ ያሉብንን ከፍተቶች በጥልቀት ያየንበትና ሁላችንንም ክፍተታችን የቱ ጋር እንደሆነ የገመገምንበት ስልጠና ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ወደስራችን ስንመለስ በአዲስ መንፈስ ያሉብንን ክፍተቶች ሁሉ ሞልተን ለተቋማችን የበኩላችንን አበርክቶ እንወጣለን ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ተቋሙ ሞዴል ተቋም ይሆን ዘንድ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ቁርጠኝነቱም እንዳለ ጠቁመው ለዚህም ደጋፊ የስራ ሂደቶችን እና ዋና የስራ ሂደቶችን በእኩል እይታ መመልከት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ያለንን ሀብት በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር ተገቢ በመሆኑ የውስጥ ኦዲት ጉድለታችንን እንድናርም ክፍተታችንን እንድናስተካክል ስልጠናው ትልቅ ሚና አለው፡፡ እናንተም የተቋማችን ባላደራ ሆናችሁ ልትቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

ስልጠናውን ለሰጡት ባለሞያዎችና ለስልጠናው አስተባባሪዎች እንዲሁም ለፕላን ኢንተርናሽናል ስላደረጉት አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበው ሰልጣኞችም ስልጠናውን ወደተግባር በመቀየር የድርሻቸውን እንደሚወጡ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡