የባለስልጣኑ ሴቶችና ህፃናት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ማርች 8 የሴቶች ዓለም አቀፍ ቀንን እኔም የእህቴ ጠባቂ ነኝ በሚል መሪ ቃል አመራሩና ሰራተኛው በአዳማ ከተማ በደማቅ ስነስርዓት አከበረ፡፡ በእለቱም በአለም የሴቶች ቀን እንዲከበር መነሻ የሆኑ፤ ታሪካዊ ዳራ የሚገልፅ ፅሁፍ በክፍሉ ዳይሬክተር ወ/ሪት ፀሃይ ሽፈራው የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም በዓሉን ስናከብር በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው አለመረጋጋት በሴቶችና ህፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃቶች በመከላከልና ድጋፍ በማድረግ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባስተላለፉት መልዕክት የሴቶች ጥያቄ የፍትህ፣ የእኩልነት እንዲሁም ከሌሎች በልጦ የመገኘት ሳይሆን ከወንዶች እኩል መብታቸው እንዲከበር የመጠየቅ መብት መሆኑን በመጥቀስ የኤ.ፌ.ደሪ ህግ-መንግስት እንቀፅ 35 ሴቶች ህግመንግስቱ ባረጋገጠላቸው መብቶችና ጥበቃዎች ከመጠቀም አንጻር ከወንዶች እኩል መብት እንዳላቸው ያረጋግጣል ይህም የዘመናት ጥያቄያቸው መልስ ያገኘበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

አያይዘውም ሴቶችን የሚጨቁኑ ወይም በአካላቸው ላይ እንዲሁም በአእምሮአቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ህጎች፣ ስርዓቶችና ልምዶችን የተከለከሉ መሆኑንም ህግ መንግስታችን በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ የሴቶችን እኩልነት በተገቢው መንገድ በህገ-መንግስታችን ሙሉ በሙሉ የተቀመጠ መሆኑን በማስታወስ ወንዶችም በአጋርነት የሴቶችን እኩልነት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል ፡፡  ሌላው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ስናከብር በርካታ ነገሮችን እናስታውሳለን ይህም በሃገራችን በሰሜኑ ክፍል የተከሰተው ጦርነት በሴቶችና ህፃናት ላይ በርካታ መከራና ስቃይ ማድረሱን በመጥቀስ ይህንንም በማዘን ብቻ ሳይሆን ሊደግፍ የሚችል ተግባራትን በማከናወን የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል በማለት ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም የዘንድሮውም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሚከበረው የተጎዱ ሴቶችና ህፃናት ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን ሴቶች ደግሞ እውቅና በመስጠት ይሆናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋ፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች፣ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ፕሮግራሙን በመደገፍ እገዛ ላደረጉ ኮንሰር እና አዲስ ህይወት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምስጋናውን አቅርበዋል፡፡