ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከኢንተር ሚኒስትሪያል ታስክ ፎርስ ሴክሬተሪያት (Inter ministerial task force secretariat) ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር ባጠኑት ጥናት የተመላከቱ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ መንግስት እየወሰደ ያለውን ርምጃ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ማብራሪያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት መንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማሳተፍ በርካታ ስራዎች እየሰራ ይገኛል በማለት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በማሻሻል ረገድ ሀገራችን ምን ላይ ነች በሚለው ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሀሳብ መስጠትና መስራት የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡
መንግስት በሁሉም ዘርፍ ለመድረስ ውስንነት ይገጥመዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ውስንነት ለመቅረፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከግሉ ሴክተር ጋር በመቀናጀት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የኢንተር ሚኒስትሪያል ታስክ ፎርስ ሴክሬተሪያት (Inter ministerial task force secretariat) ዶ/ር ታደሰ ካሳ በመንግስት በኩል ጥናቱን መሰረት በማድረግ መንግስት እየወሰደ ያለውን ርምጃ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ተወካዮች ያብራሩ ሲሆን የታስክ ፎርሱ አወቃቀርና የስራ እንቅስቃሴ ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡ የውይይት መድረኩን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ካውንስል በተገኘ የፋይናንስ ድጋፍ ያዘጋጀው ነው፡፡