የተቋሙ የሴቶች ፎረም የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያና አዲስ የፎረም አባላትን የመመዝገብ ስነስርዓትም ተካሂዷል፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ባዘጋጀው በዚህ የስልጠና መርሃ ግብር ላይ የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ሲኒየር ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉሱ ተገኝተዋል፡፡ ስልጠናው በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው በማህፀን በር እና በጡት ካንሰር ላይ ሲሆን ዓቢይ ዓላማውም የተቋሙ ሴት ሰራተኞች ስለማህፀን በር ካንሰር አስከፊነት ግንዛቤ ወስደው ቅድመ የማህፀን በር ምርመራ በማድረግ ከዚህ አስከፊ በሽታ ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡

የባለሥልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በስልጠናው ማስጀመሪያ ወቅት እንደተናገሩት ጤና በእጃችን ሳለ ብዙ ትኩረት የማይሰጠው፤ ስናጣው ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ገልፀው ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን የጤናችንን ጉዳይ ልንከታተል ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሁላችሁም እንደምታውቁት ቀደም ባለው አዋጅ የተነሳ ድርጅቶች ወደኛ ለመቅረብ ይቸገሩ እንደነበር አንስተው አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ከወጣ ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ግን የህግ መሻሻል ብቻ ሳይሆን ድርጅቶችና አጋር አካላት ለተቋማችን ያላቸው አመለካከት እየተሻሻለና እየተቀየረ መጥቷል፤ በዚህም የተነሳ ነው ከድርጅቶች ጋር በመተባበር መሠል ስልጠናዎች እየተዘጋጁ ያሉት ብለዋል፡፡ ለአንድ ተቋም ስኬት የሰው ኃይል ትልቅ ትልቅ ሚና አለው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ክህሎት ያለው፣ በዕዉቀት የዳበረ፣ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሰ ቅንነት ያለው ሰራተኛ ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ ተቋሙም ሞዴል ተቋም እንዲሆንና ቀልጣፋና አርኪ ስራዎችን ለመስራት የተቋማችን ሰራተኞች ጤናማ፣ ስነ ምግባርን የተላበሱ ታታሪ ሰራተኞች እንዲኖሩን ይገባል፤ በተቋማችን ያሉ ሴት አመራሮችም እጅግ ስኬታማና ስራቸውን የሚያከብሩ በመሆናቸው ባለሥልጣን መስሪያ ቤታችን ያመሠግናቸዋል ሲሉ አክለው ገልፀዋል፡፡

የፖዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ሲኒየር ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉሱ በበኩላቸው ፓዝ ፋይንደር እ.ኤ.አ ከ1966 ጀምሮ ፓስ ፋይንደር ፈንድ በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ መሠረቱን የጣለ ድርጅት መሆኑን አንስተው ለረጅም አመታት በስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል፡፡ የማህጸን በር ካንሰር በዓለም ላይ አደገኛ ከሆኑ በሽታዎች በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነ ጠቁመው ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ ከ15-20 አመት ሊቆይ ይችላል ብለዋል፡፡ አክለውም በሽታውን ስር ሳይሰድ መከላከል እንደሚቻልና ማንኛዋም ሴት በየ5 አመት ልዩነት በመመርመርና ህክምና በመውሰድ በሽታውን መከላከል እንደምትችል አንስተው ድርጅታቸው ከ2019ዓ.ም ጀምሮ ሲንግል ቪዚት አፕሮችን በመከተል ሴቶች አፋጣኝ ህክምና እንዲያገኙ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በቅርበት በርካታ ስራዎችን ሲሰሩ እንደቆዩ ያነሱት ዳይሬክተሩ መሠል ስራዎችን ወደፊትም አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በዕለቱ የሴቶች ፎረም ውስጠ ደንብ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ተቋሙን ለተቀላቀሉ አዲስ የሴት ሰራተኞች ፎረሙን የማስተዋወቅ ስራ ተከናውናል፡፡ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ጸሀይ ሽፈራው ፎረሙን ባስተዋወቁበት ወቅት ተቋሙ ለሴት ሰራተኞች ልዩ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝና ከ30% በላይ የሚሆኑት ሴት አመራሮች እንደሆኑ አንስተው የተቋማችን ሴት ሰራተኞች እጅግ ምስጉንና ውጤታማ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ይህ የሴቶች ፎረም ሴቶች ልዩ ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ፤ በርካታ ሴቶችም ወደ አመራርነት እንዲመጡ ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ሴቶች ማንኛውም በስራ ላይ የሚገጥማቸው ችግር ካለ በማስረጃ ቢያቀርቡልን አፋጣኝ መልስ እንዲያገኙ ፎረሙ ከፍተኛ ስራ የሚሰራ ይሆናል ሲሉም አክለው ገልፀዋል፡፡ በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ለፓስ ፋይንደር ኢንተርናሽናል የምስጋና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ለተቋሙም ሴት ሰራተኞች የእንኳን ደህና መጣችሁ ስጦታ በፎረሙ በኩል ተበርክቶላቸዋል፡፡