ጉባኤው ዶ/ር ገዛኸኝ ከበደ ሰብሳቢ እና አቶ ያሬድ ሃይለማርያም ጸሐፊ አድርጎ መርጧል፡፡ በምስረታ ጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት መንግስታዊ ተቋማት ለሕዝቡ የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ውጤታማና በአገልጋይነት መንፈስ ይተገበር ዘንድ፣ በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቀጣይነት ለመፍታት፣ለተገልጋዮች የሚሰጠውን አገልግሎት በሚፈለገው የጥራት ደረጃ በማቅረብ የተገልጋይን እርካታ ማሳደግ፣ ንቁ ተሳትፏቸውን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማጎልበት እንዲቻል እና አደረጃጀት ለመፍጠርም ይህ የመማክርት ጉባኤ መቋቋሙ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለሕዝቡ ቃል ከገባባቸው ጉዳዬች መካከል አንዱ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን በማሻሻል ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ፈጣን፤ቀልጣፋ፤ውጤታማና ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠትና የሕዝቡን የአገልግሎት እርካታ ማሳደግ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የተገልጋዩን ፍላጎት ያማከለ አገልግሎት መስጠት ይቻል ዘንድ መንግስት ከሚያርገው ጎን ለጎን የህዝብ እና የተገልጋይ ተሳትፎን ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በኩል የህዝብ ተሳትፎን ለማጠናከርና የሕዝብ አገልጋይነት አመለካከት ለማስረጽ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሚሆንበት የመማክርት ጉባኤ ማቋቋሚያ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
ተቋማችንም የለውጡ ውጤት ከሆኑና የህዝብን አገልጋይነት ባህልን ለማሳደግ በጽናት ከሚሰሩ መንግስታዊ ተቋማት መካከል አንዱ እንደመሆኑ መጠን ይህ የመማክርት ጉባዔ እንዲቋቋም አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ ሰነዱን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የአገልግሎት ጥራት ክትትልና ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ድንገታ ያቀረቡ ሲሆን የጉባኤው ዓለማ አደረጃጀት፣ተግባርና ሃላፊነትና ውክልናን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም በተቋሙ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የጉባኤው አባላት 42 ሲሆኑ 64.29 % ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ከተቋሙ ዋና የስራ ሂደት 16.67 % እና ከፌደራል ባለድርሻ የመንግስት ተቋማት 19.04 % ድርሻ ያለው ነው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በተመለከተ ሴቶችን፣ወጣቶች፣አካል፣ጉዳተኞችን፣አረጋዊያንን እና ሌሎች አደረጃጀቶችን ታሳቢ ያደረገ ነው ፡፡ በመጨረሻም ጉባኤው 7 ስራ አስፈጻሚ አባላትን የመረጠ ሲሆን ዶ/ር ገዛኸኝ ከበደ ሰብሳቢ በማንዋሉ መሰረት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ም/ሰብሳቢ እና አቶ ያሬድ ሃይለማርያም ጸሐፊ ሆኖ የተቀሩት 4ቱ አባል በመሆን ይሰራሉ፡፡