የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ በመገኘት ወራሪውን የትግራይ ቡድን ለመመከት በግንባር ሲዋደቁ የነበሩ አርሶ አደር ዘማቾችን ሰብል ሰብስበዋል፡፡ በዚህ የሰብል ስብሰባ መርሃ ግብር ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪና የወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ወራሪው ቡድን በርካታ ወንጀሎችን ሲሰራ ቆይቷል፤ እኛም ስንመክት ቆይተናል ያሉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፤ ይህ ወራሪ ቡድን የቃጣብንን ጥቃት መላው ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመነቃነቅና በጋራ በመሆን ከወረራቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች ተጠራርጎ እንዲወጣ በማድረግ ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርገዋል ብለዋል፡፡ ማክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አሸባሪ ቡድኑ ዳግም እንዳይነሳና መልሶ ወረራ እንዳይፈጽም እስከወዲያኛው የማጥፋት ስራ በመንግስት በቀጣይ የሚሰራበት መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለው የሚያስቡ  የውስጥም የውጪ ጠላቶችን ያሳፈረ፤ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የማትፈርስ ሀገር መሆኗንና የትኛውም ችግር ቢመጣ ኢትዮጵያውያን የውስጥ ችግሮቻቸውን ወደጎን በመተው ለጋራ አላማቸው የሚሰለፉ መሆናቸውን ያስመሰከሩበት ድል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በንግግራቸው እንደገለጹት አጋጣሚው ኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግንኙነታችንን እንድናጠናክር እድል ሰጥቶናል፤ በርካታ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች አሉብን፤ ጥቃቅን የሆኑትን የዘርና መሰል የሆኑ ልዩነቶቻችንን ትተን በጋራ ከሰራን ፖለቲካውንም ኢኮኖሚውንም እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብራችንን ማስተካከል የምንችል መሆኑን ያየንበት ነው፡፡ ጠላቶቻችን እርስ በርስ ይበላላሉ፤ ይጫረሳሉ ብለው ለ30 አመታት የሰሩልንን የልዩነት ግንብ ትተን የአንድነት ግንብ የሰራንበት ወቅት ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ይህን ጦርነት ለመመከት ግንባር ድረስ በመዝመት ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ የነበሩትን የሞረትና ጅሩ ወረዳ ሚሊሻዎችን ሰብል ለመሰብሰብ ከመሃል አዲስ አበባ ድረስ ስንመጣ አንድ መሆናችንን፤ የእናንተ ጉዳት የእኛም ጉዳት ነው ለማለትና ሁልም ቢሆን ኢትዮጵያውያን ከጎናችሁ ነን ለማለት ነው፡፡የወደመውን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድቀቶችን የማስተካከል ብዙ የቤት ስራዎች ይጠበቁብናል፡፡ጦርነቱ አሁን ባለበት ሁነኔታ የኛ መፈክር ሊሆን የሚገባው እናልማ፣እንገንባ፣ እንዘጋጅ ነው፡፡ ኢኮኖሚያችንን መልሶ ለመገንባት መረባረብ ያለብን ወቅት ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ዛሬ መጥተን እንዳየነው በሚያስደንቅ ሁኔታ አደለም ይህን ወረዳና ዞን ድፍን ኢትዮጵያን መመገብ የሚችል ትልቅ የእርሻ አቅም ያለው መሆኑን አይተናል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የግብርና ምርታችን አመርቂ የሚባል ነው፡፡ የወደሙ ከተሞችን መልሶ በመገንባትም ከፍተኛ ርብርብ ማድርግ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው፡፡ ዛሬ እዚህ የተገኘንበት አንዱና ትልቁ ምክንያትም ለእኛ ሲሉ ነው ግንባር ድረስ ዘምተው የቆሰሉት፣ የተጎዱት፣ ብለን ህመማቸው ህምማችን ቁስላቸው ቁስላችን መሆኑን ለመግለጽ ስንመጣ ሀብታቸውን በመሰብሰብ ኢኮኖሚያቸው ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል የበኩላችንን አስተዋጽዖ እያበረከትን ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡ ጦርነቱ ገና ነው አላለቀም፡፡ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ጠላት የማይበገር ሰራዊት መገንባት፤ ስለሰላም እየሰበኩ ጎን ለጎን መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ አንድነታችንን እናጠናክር ለዚህም ነው ወደዚህ የመጣነው፡፡የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በስሩ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን በማስተባበር በአንድ ቀን ጥሪ ብቻ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ለተጎጂ ወገኖቻችን አሰባስበናል፤ በቀጥታም ለተጎጂዎች እንዲደርስም እያደረግን ነው፡፡ ለተቋሙ ሰራተኞች በቢሮ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ ብዙ መንገድ አቋርጣችሁ ለዘማቾቹ አለን ከጎናችሁ ነን በማለታችሁ እጅግ የከበረ ምስጋናየን አቀርባልሁ ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸል፡፡

የሞረትና ጅሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳ አቶ ሙሉጌታ በበኩላቸው ወረዳው በስንዴና በጤፍ እንዲሁም በጥራጥሬ ሰብሎች በምስርና በባቄላ የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመው ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩም የአካባቢውን የሰብል ሀብት መጥተው የጎበኙት እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ወራሪው የህውኃት ቡድን ይህን አካባቢ ለማጥፋት አጎራባች ወረዳዎች ድረስ ተጠግቶ ነበር ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በመላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ ወደመጣበት እንዲመለስ ተደርጓል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ይህ አካባቢ መደገፍ ይገባዋል ብላችሁ ብዙ ኪሎሜትር አቋርጣችሁ በመምጣታችሁ እንዲሁም ሰራተኛ ጭምር ቀጥራችሁ የዘማቾችን ስለሰበሰባችሁና ድጋፍ ስላደረጋችሁልን ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለሁለተኛ ጊዜ ባደረገው በዚህ የሰብል መሰብሰብ መርኃ ግብር ከ3.5 ሄክታር በላይ በስንዴና በጤፍ የተሸፈነ ሰብል የተሰበሰበ ሲሆን በወረዳው ለችግር ለተዳረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ይሆን ዘንድ የተለያዩ አልባሳትንም ለወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ አስረክበዋል፡፡